ኢንስቲትዩቱ የ2017 ዓ.ም በጀት አመት የመጀመሪያ ስድስት ወር እቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ አካሄደ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2017 ዓ.ም በጀት አመት የመጀመሪያ ስድስት ወር እቅድ አፈፃፀም ግምገማ የካቲት 13 በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዷል።
በዚህ የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዩጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በተያዘው በጀት ዓመት በመጀመሪያ ስድስት ወራት ለማከናወን የታቀዱ እቅዶቹን ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ባለ ድርሻ አካላት እንዲሁም በየዘርፉ ከሚገኙ ባለ ድርሻ አካላት ጋር እቅድ የማናበብ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
ተቋሙ በህዝብ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ዘርፈ ብዙ የሕብረተሰቡን ጤና የሚያስጠብቁ ስራዎችን በቅንጅት በመስራት ውጤት ያስመዘገበበት ወራት መሆኑንም ገልፀዋል።
ግማሽ በጀት አመቱ ጠንካራ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና ምላሽ መስጠት ስራዎች በስፋት የተከናወኑበት መሆኑንም ገልፀዋል።
በቀጣይ በሚኖሩ ጊዜያት እቅዶችን በመከለስ ታቅደው ያልተከናወኑ ተግባራትን በመለየት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በኃላፊነት በመስራት የሕብረተሰቡን ጤና ሊያስጠብቅ የሚችል ስራ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
በዚህ የግምገማ መድረክ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ፣ ዶ/ር ሳሮ አብደላ እና ዶ/ር መልካሙ አብቴ እንዲሁም በኢንስቲትዩቱ ስር ያሉ ዳይሬክቶሬቶች፣ የጽ/ቤት ኃላፊዎች እና የቡድን መሪዎች ተገኝተዋል።
በኢንስቲትዩቱ ስር ያሉ እነዚሁ ዳይሬክቶሬቶች በ2017 ዓ.ም ግማሽ አመት አቅደው ያከናወኗቸውን ጠንካራና መሻሻል የሚሹ የተግባራት ሂደቶችን በሪፖርት አቅርበዋል።
ዳይሬክቶሬቶቹ ባቀረቧቸው የእቅድ ክንውን ሪፖርቶች ላይ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው በዳይሬክተሮች፣ በምክትል ዳይሬክተሮችና በዋናው ዳይሬክተር ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።