ዓመታዊ የጊኒ ዎርም በሽታ የማጥፊያ ፕሮግራም የአፈጻፀም የግምገማ መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል

ክቡር ዶ/ር ጋትሉዋክ ሮን የጋምቤላ ህዝብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር፣ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በተገኙበት ዓመታዊ የጊኒ ዎርም በሽታ የማጥፊያ ፕሮግራም የአፈጻፀም ግምገማ እና የምክክር መድረክ በሀገራችን ለ29ኛ ጊዜ የካቲት 20 እና 21/2017 ዓ.ም በጋምቤላ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የጋምቤላ ሕ/ክ/መ/ም/ ርዕሰ-መስተዳድርና የከተማ መሰ/ልማት ቢሮ ሀላፊ ክቡር ዶ/ር ጋትሉዋክ ሮን የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት የጊኒ ዋርም በሽታን ከአገራችን ለማጥፋት ላለፉት 30 ዓመታት መጠነ ሰፊ ጥረቶች ቢደረጉም በተለያዩ ምክንያቶች በሽታው በክልሉ እስካሁን ማጥፋት እንዳልተቻለና በአሁኑ ወቅት የጊኒ ዋርም በሽታ በክልሉ አኙዋሃ ብሔረሰብ ዞን በጎግና በአበቦ ወረዳዎች በእንስሳት ላይ በተለይም በዝንጀሮ፣ በውሻና ድመት ላይ በተደጋጋሚ እየተከሰተ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የማጥፋት ዘመቻ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ደ/ር ደረጄ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በመድረኩ ተገኝተው እንደገለጹት ኢትዮጵያ የጊኒ ዎርም የማጥፊያ ፕሮግራም እ.ኤ.አ ከ2018 እስከ 2025 ባሉት ጊዜ አመርቂ ዉጤቶችን ማስመዝገቧን ጠቁመው በቀጣይም የጊኒ ዎርም በሽታን ጨርሶ ለማጥፋት ደህንነቱ የተጠበቀ የውሃ ምንጮችን ማስፋፍት፣ ኩሬዎችን መለየት እና በተገቢዉ መንገድ ማከም፣ የቤት እና የዱር እንስሳት ላይ ያለዉን ቅኝት ማጠናከር፣ የማህበረሰብ ተሳትፎን በማጠናከር የተሻለ የህዝብ ንቅናቄ መፍጠር እንዲሁም በአንድ ጤና ስርዓት መሰረት(One Health) ስራዎችን ከማጠናከርም በላይ የምርምርና እና ጥናት ስራዎችን በማስፋት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ማብራሪያ ስጥተዋል፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የጊኒ ዎርም በሽታ ከአገራችን ለማጥፋት ለሦስት አሥርት ዓመታት በርካታ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎች መሰራታቸውን በመገለጽ የማጥፋት ፕሮግራም ከተጀመረ ጀምሮ 4,697 ሰዎች፣ 64 ዉሻዎች፣ 14 ድመቶች እንዲሁም 23 ዝንጄሮዎች በበሽታው መያዛቸውን፣ በተደረገው ከፍተኛ ቅንጅታዊ የመከላከል ርብርብ በ2023 እ.ኤ.አ እና 2024 እ.ኤ.አ በሽታው በሰዎች ላይ እንዳይከሰት ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፤ ዝንጀሮን ጨምሮ በእንስሳት ላይ እየተከሰተ ያለዉ የጊኒ ዎርም በሽታ ከምንም ጊዜ በበለጠ የቁጥጥር እና ምላሽ ስራዎችን በቅንጅት እና በመናበብ ከኢትዮጵያ ጨርሶ ለማጥፋት በትጋት መሰራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የጋምቤላ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የአጋር ድርጅት ተወካዮች በመድረኩ ተገኝተው የጊኒ ዎርም በሽታ የማጥፊያ ፕሮግራሙን አስመልክቶ የየራሳቸውን መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በምክክር መድረኩ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት ከዚህ ዓለም ህይወታቸው ያለፉትን የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጂሚ ካርተርን በጸሎት በማሰብ የተከፈተ ሲሆን ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬተር እና የኢንስቲትቱ የተለያዩ የስራ ክፍል ኃላፊዎች፣ የግብርና፣ የውሃ፣ የጤና ሚኒስቴር ተወካዮችና የአጋር ድርጅት ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማነት፣ የነበሩ ተግዳሮቶችን እንዲሁም በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት፣ የመፍትሄ ስራዎችን በመለየት እና የጋራ መግባባት በመፍጠር የቀጣይ አቅጣጫን በማስቀመጥ የምክክር መድረኩ የሚጠናቀቅ መሆኑን ከመደረኩ አስተባባሪዎች መገንዘብ ተችሏል፡፡