የሕብረተሰብ ጤና የመልካም አሰተዳደር ክትትልና ምዘና ማዕቀፍ ረቂቅ ዝግጅት አውደ ጥናት በመካሄድ ላይ ነው

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተቋማዊ ለውጥ ስራ አስፈጻሚ የሕብረተሰብ ጤና የመልካም አሰተዳደር ክትትልና ምዘና ማዕቀፍ ረቂቅ ዝግጅት ከታህሳስ 7 እስከ 10/2017 ዓ.ም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች በተገኙበት በአዳማ ከተማ አውደ ጥናት በማካሄድ ላይ ነው፡፡
የረቂቅ ማዕቀፍ አውደ ጥናት ዝግጅቱ ዋና ዓላማ የሕብረተሰብ ጤና የመልካም አስተዳደር የክትትል እና ምዘና ማእቀፍ በማዘጋጀት በተቋሙ የሚወሰኑ የተለያዩ ውሳኔዎች መረጃና ማስረጃ ላይ መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ ለማድረግ፤ በተቋሙ የሚሰጡ ማንኛውም አገልግሎቶች ቀልጣፋ እና ውጤታማ እንዳይሆኑ የሚያደርጉ ተግዳሮቶችን ነቅሶ ለማውጣት እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ይቻል ዘንድ የመጀመሪያ ረቂቅ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት ነው፡፡
ወ/ሮ ሐረገወይን መንክር የተቋማዊ ለውጥ ስራ አስፈጻሚ ከፍተኛ ባለሙያ በአውደ ጥናቱ ፕሮግራም ላይ የመልካም አሰተዳደር ክትትልና ምዘና ማዕቀፍ ዝግጅቱን አስመልክቶ የመልካም አስተዳደር ምንነት፣ የመልካም አስተዳደር ክትትልና ምዘና ማዕቀፍ የሚያካትታቸውን ጉዳዮች ወይም መነጽር የተባሉትን የሕግ የበላይነት፣ ፈጣን ምላሽ፣ ቀልጣፋና ውጤታማነት፣ የጋራ መግባባት፣ ተጠያቂነት፣ ግልጽነት፣አካታችነትና ፍትሐዊነት እንዲሁም አሳታፊነት የሚሉትን በዝርዝር በጽሁፍ በማቅረብ ማዕቀፉ መዘጋጀቱ ለአንድ ተቋም የመልካም አስተዳደር መስፈን የሚሰጠውን ከፍተኛ ጠቀሜታ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በሕብረተሰብ ጤና ዘርፍ እና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስፈልጉ መለኪያዎች (GGI Indicators) በማስቀመጥ በየዘርፉ የተለዩ ችግሮች የሚፈቱበት ስርዓት ከክልል እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ከመዘርጋት አንጻር የሚሰሩ ስራዎች ምን እንደሚመስሉ በመድረኩ ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡
የተለያዩ የክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ያላቸውን ልምድ የሚያካፍሉ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር የክትትል እና ምዘና እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የተቋማት ማዕቀፍ በመዳሰስና በመነሻነት በመጠቀም የኢንስቲትዩቱን የመልካም አስተዳደር የክትትል እና ምዘና ማዕቀፍ የመጀመሪያ ረቂቅ የሚዘጋጅ ሲሆን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና አንስቲትዩት እና የክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች በአውደ ጥናቱ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡