የምርምር ውጤቶችን ወደ ፖሊሲና ተግባር በመቀየር የሕብረተሰብ ጤናን ለማሻሻል የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረዋል

የምርምር ውጤቶችን ወደ ፖሊሲና ተግባር በመቀየር የሕብረተሰብ ጤናን ለማሻሻል የሚደረጉ ጥረቶች እየተጠናከሩ መሆናቸው ተገለጸ
——————————-
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥርዓተ-ምግብ፣ አካባቢ ጤናና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ከሐምሌ 22 እስከ 23 ባደረገው የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ በቀረቡት የምርምር ስራዎች ሪፖርት ላይ የምርምር ውጤቶችን ወደ ፖሊሲና ተግባር በመቀየር የሕብረተሰብ ጤናን ለማሻሻል የሚደረጉ ጥረቶች እየተጠናከሩ መሆናቸው ተገልጿል።

የምርምር ሥራዎች ውጤታማነት በህትመት ብዛት ብቻ ሳይሆን በፖሊሲ፣ በጤና ሥርዓትና በሕብረተሰቡ ጤና ላይ በሚያመጡት ተጨባጭ ለውጥ ላይ መሰረት ያደረገ ሲሆን ነው በማለት በመድረኩ ላይ የተናገሩት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የምርምር ውጤቶች ለውሳኔ አሰጣጥ የሚያገለግሉ ማስረጃዎች እንዲሆኑና ወደ ተግባር እንዲሸጋገሩ በተቀናጀ ሁኔታ መሰራት እንዳለበት በማስታወስ በዚህ ረገድ ዳይሬክቶሬቱ እየሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ ነው ብለዋል። በተጨማሪም በመተማመንና በትብብር የሚከናወኑ ሳይንሳዊ ሥራዎች ለሀገር እድገት ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ፣ የቡድን ሥራን የተቋሙ የሥራ ባህል እንዲሆን አደራ ብለዋል።
የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ማስረሻ ተሰማ በበኩላቸው፣ በ2018 በጀት ዓመት 50 የምርምር ጥናታዊ ጽሑፎች እንደ ላንሴት ባሉ ዓለምአቀፍ የጤና መፅሔት ላይ ለህትመት መብቃታቸውን ገልጸው፣ ይህም የተመራማሪዎች ጠንካራ የሥራ መንፈስና የቡድን ትብብር ውጤት ብቻ ሳይሆን የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅና ለማሻሻል የተደረገውን ከፍተኛ ሳይንሳዊ ጥረት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል። የምርምር ውጤቶቹም በጤና ፖሊሲና በአሠራር ላይ ተጨባጭ ለውጦችን እያመጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመድረኩ የዳይሬክቶሬቱ የዲቪዥን መሪዎች በየዘርፋቸው ያከናወኗቸውን የምርምር ሥራዎች አቅርበው በሰፊው ውይይት አድርገዋል። ከቀረቡት ውጤቶች መካከል የጥቃቅን ንጥረ-ምግቦች ጥናት፣ የኢትዮጵያ ምግቦች የንጥረ-ነገር ይዘት ምርምር፣ የEthiopian Food System Database ዲጂታል መረጃ ሥርዓት ልማት፣ እንዲሁም በፎሊክ አሲድና በአዮዲን የበለፀገ ጨው አጠቃቀም አማካኝነት የነርቭ ዘንግ ክፍተትን ለመቀነስ የተካሄዱ ጥናቶች ፣ በከባቢ አየር፣ በተለይም ወንዞችና የውሀ አጠቃቀም ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶች ለሀገሪቱ የጤና ፖሊሲ ማሻሻያ ግብዓት መሆናቸውና በዚህም ሥራ እየመጡ ያሉ ለውጦች አበረታች መሆናቸው ተገልጿል።
በመጨረሻም በሪፖርቶቹ ላይ የተካሄደውን ውይይት ተከትሎ፣ የምርምር ጥራትን ማሳደግ፣ የምርምር ውጤቶችን ወደ ፖሊሲና ተግባር በፍጥነት መቀየር፣ የትብብር አጋርነትን ማጠናከር፣ የተመራማሪዎችን አቅም ማሳደግ እና የላቀ የምርምር ሥራ ለሚያከናውኑ ተመራማሪዎች እውቅና በመስጠት የልህቀት ባህልን ማጎልበት ትኩረት ተሰጥቶባቸው እየተሰራባቸው መሆኑ ተጠቁሟል።