የቲቢ ምርመራን የሚያሻሽል አዲስ የሞለኪዩላር ቲቢ ምርመራ ማሽን ይፋ ተደረገ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴርና ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር የቲቢ ምርመራን የሚያሻሽል አዲስ የሞለኪዩላር ቲቢ ምርመራ ማሽን ይፋ አድርጓል።

የሞሎኪውላር ቲቢ ምርመራ ማሽንን ይፋ የማድረጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ፣ ቲቢን በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግሥት በሰፊው እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ በአገሪቱ ከ1,000 በላይ የGeneXpert ማሽኖች መሰራጨታቸውን አስታውሰዋል። አዲሱ የሞለኪዩላር ማሽን በተለይ በመጠለያ ጣቢያዎች፣ በማረሚያ ቤቶች፣ በማዕድን ማውጫዎችና በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦች የምርመራ አገልግሎት ተደራሽነትን በእጅጉ እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፣ ኢንስቲትዩቱ የላቦራቶሪ አቅምን በማጠናከር፣ የሕብረተሰብ ጤና ምርምርን በማስፋትና ከጤና ሚኒስቴር፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከአጋር ተቋማት ጋር በመቀናጀት የቲቢ መከላከልና ቁጥጥር ሥራዎችን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። አዲሱ ቴክኖሎጂ በጤና ጣቢያዎች በሰፊው ተደራሽ ሲሆን በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ላቅ ያለ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ዶ/ር ሕይወት ሰለሞን በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ በበኩላቸው አዳዲስ የሚተዋወቁ ፕሮግራሞችን አስመልክቶ የባለሙያዎችን አቅም መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ የሞለኪዩላር ቲቢ ምርመራ ማሽን ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የKNCV ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አህመድ በድሩ በበኩላቸው፣ ለታካሚው ቅርብ የሆኑ ተንቀሳቃሽ የሞለኪዩላር ምርመራ ቴክኖሎጂዎች የላቦራቶሪ መሠረተ ልማት ውስን በሆኑ አካባቢዎችም ፈጣንና ትክክለኛ የቲቢ ምርመራ ለመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ የተገለጸው መረጃ እንደሚያሳየው፣ 268 የሞለኪዩላር ቲቢ ምርመራ ማሽኖች በ134 ጤና ጣቢያዎች እንዲገጠሙ የታቀደ ሲሆን በቀጣይም ተጨማሪ 3,000 የምርመራ ማሽኖችን በመግዛት በመላ አገሪቱ ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን በጤና ሚኒስቴር የቲቢ ፕሮግራም የላቦራቶሪ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ጌታቸው አጋ ገልጸዋል።