የኢንስቲትዩቱ የምርምር ስነ-ምግባርና የሕትመት ጽ/ቤት እውቅናው ሊታደስ ነው

በኢንስቲትዩቱ የምርምር ስነ-ምግባር፣ የሕትመት ጽ/ቤት እና የኢንስቲትዩቱ የምርምር ስነ-ምግባር ግምገማ ቦርድ (IRB) አስተባበሪነት ዓለም ዓቀፍ የምርምር ሥነ-ምግባር ግምገማ (Systematic Initiative for Developing Capacity in Ethical Review (SIDCER)) ቦርድ በፕሮፌሰር ጁንትራ ካርብዋንገግ የሚመራ ልኡክ የኢንስቲትዩቱ የምርምር ስራዎች ዓለም ዓቀፍ መስፈርቶችን ተከተሎ እየሰራ መሆኑን በመከታተል እውቅናውን ለማደስ የተቋሙን ስራዎች ቅኝት እያደረጉ ነው፡፡

ዓለም ዓቀፍ የምርምር ሥነ-ምግባር ግምገማ ቦርድ በጤና እና በባዮሜዲካል ምርምሮች ላይ የሚደረግ የሥነ-ምግባር ምዘና SIDCER በዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ድጋፍ የተቋቋመ ዓለም አቀፍ ቦርድ ነው፡፡ የቦርዱ የቅኝት ዓላማ የኢንስቲትዩቱን የምርምር ጽሁፎችን እና መሰል ስራዎች በምርምር ስነ-ምግባራዊ ይዘቶች ዓለም ዓቀፍ መስፈርቶችን ያሟላ መሆኖን በመገምገም እና በማረጋገጥ እውቅና ለማደስ ነው፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ልኡካኑን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያቀረቡ ሲሆን አጠቀላይ የኢንስቲትዩቱን ኃላፊነትና ድርሻ በዝርዝር የገለጹ ከመሆኑም በላይ ኢንስቲትዩቱ እንደ ዋና የጤና ሚኒስቴር ሳይንሳዊ እጅ በመሆኑን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሕብረተሰቡን ጤና በማስጠበቅ በኩል ከበሽታ ክትትል እስከ ድንበር ጤና ድረስ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ ኢንስቲትዩቱ በአፍሪካ ከሚገኙ ታዋቂ የሕብረተሰብ ጤና ተቋማት አንዱ መሆኑንና፣ የዓለም አቀፍ የብሔራዊ የሕብረተሰብ ጤና ተቋማት ማህበር (IANPHI) የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አባል በመሆን ለሀገራዊ ጤና ትልቅ ትኩረት በመስጠት ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን ተናገረዋል።
ዶ/ር መሳይ በንግግራቸው፣ የኢንስቲትዩቱ ሕጋዊ ማዕቀፍ በተቋሙ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በክልላዊ ጤና ተቋማት፣ በዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች የምርምር ተቋማት የምርምር ሥነ-ምግባርን ለማጠናከር ጠንካራ መሠረት መጣሉንም አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የምርምር ሥነ-ምግባርና የሕትመት ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር ማሕደር ሚሊዮን ለልኡካኑ ስለ ኢንስቲትዩቱ ራዕይ፣ ተልእኮ፣ አደረጃጀት፣ የምርምር ሕትመቶች እና የተካሄዱ ሳይንሳዊ ጉባኤዎች ዝርዝር ገለጻ አቅርበዋል።
በመጨረሻም የSIDCER ልኡካን በኢንስቲትዩቱ የሚያከናውኑትን የግምገማ ሂደት፣ የሚከተሉትን ዓለም አቀፍ መስፈርቶች እና የቆይታ መርሃ ግብራቸውን በዝርዝር ካቀረቡ በኋላ የቅኝት ሥራቸውን ጀምረዋል።