የኢንስቲትዩቱ የምርምር ዘርፍ የ6 ወራት የአፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ::

በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከአምሣ አምስት በላይ የሚሆኑ የሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶች በዓለም ላይ ከፍተኛ ተቀባይነት ባላቸው የሳይንስ ጆርናሎች መታተማቸውም ተነግራል::
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምርምር ዘርፍ የ6 ወራት የአፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ::
በመድረኩ ላይ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ ባደረጉት ንግግር፣ በስድስት ወራቱ ውስጥ በተለያዩ የጤና ዘርፎች ሀገራዊና አለምአቀፋዊ ፋይዳ ያላቸው፣ ለፖሊሲ ግብአት የሚያገለግሉ እና ጤና አገልግሎት ስራ ላይ ሚና ያላቸው በርካታ ምርምሮች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።ከአምሳ አምስት በላይ የሚሆኑ ሳይንሳዊ ምርምሮችም ከፍተኛ ተቀባይነት ባላቸው አለማቀፍ የሳይንስ ጆርናልች ላይ መታተማቸውን አስረድተዋል::
ዶ/ር ጌታቸው ለአብነት፣ የነርቭ ዘንግ (Spinal Bifida) ችግርን ለመከላከል አጋዥ የሆነውን “አይረን–ፎሊክ” የተባለ ንጥረ ነገር ከጨው ጋር ለማበልጸግ የተካሄደ ጥናት መጠናቀቁንና ይፋ መደረጉን ጠቁመዋል። እንዲሁም ለሀገሪቱ የስርዓተ ምግብ ፖሊሲ አስፈላጊ የሆነው የምግብ የንጥረ ነገር ዘንጠረዥ (Food Composition Table) መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
እንደ ንግግራቸው፣ ኢንስቲትዩቱ በስርዓተ ምግብ፣ በአካባቢ ጤና፣ በተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች፣ በጤና ስርዓት (Health System)፣ በወባና ተያያዥ ጉዳዮች ፣ ትኩረት በሚሹ ሀሩራም በችታዎች እንዲሁም በተላላፊ በሽታዎች ዙሪያ በርካታ ጥናቶችና ምርምሮች ተካሂደዋል፣ ከእነዚህም ብዙዎቹ ተጠናቀው ይፋ ተደርገዋል።
በተጨማሪም ለምርምርና ለጥናት ስራዎች አጋዥ ከሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ አጋሮች ጋር ጠንካራ ትብብር መመስረቱን የጠቁሙት ዶ/ር ጌታቸው፣ ኢንስቲትዩቱ የምርምር አቅሙን ለማጠናከር ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን፣ ብቁ ባለሙያዎችን፣ ዘመናዊ አሰራሮችንና ዕውቀትን በማቀናጀት በዘርፉ “የልህቀት ማዕከል (Center of Excellence)” ለመሆን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የስርዓተ ምግብ፣ የአካባቢ ጤና እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማስረሻ ተሰማ በቀረቡት ሪፖርት፣ ለተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የአመጋገብ መመሪያዎች ማዘጋጀትና ማዘመን፣ በሀገሪቱ የሚገኙ ምግቦች የንጥረ ነገር ይዘት ጥናት፣ የምግብ ደህንነት እንዲሁም በአካባቢ ጤና ዘርፍ የአየር ንብረት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ማስተካከልና የጤና እና የአካባቢ ተጽዕኖ ጥናቶች መካሄዳቸውን አመልክተዋል። እነዚህ ጥናቶች ለሀገሪቱ ፖሊሲ ከፍተኛ ግብአት ያላቸው መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ መድረክ የስርአተ ጤና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አደራጀው መኮንን፣ የጤና ስርዓቱን ለማጠናከር በተለያዩ መስኮች ላይ ምርምሮች መካሄዳቸውን ገልጸው፣ በባለፉት ስድስት ወራት አምስት ጠቃሚ የምርምር ውጤቶች የማሳተም ስድስት የፖሊሲ ብሪፎች እና ስድስት የሪሰርች ፕሮፖዛሎች ይፋ መደረጋቸውን እና መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።ለአብነትም ከአምስት አመት በታች በሆኑ ህጻናት የሚከሰተውን አጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት ችግር ለመፍታ የሚያስችል ጥናት እንዲሁም ለእርጉዝ እናቶች የሚሰጣቸውን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል እና ሌሎች ጥናቶችን ማከናወኑንም አክለው ገልጸዋል::
የወባ እና የተዘነጉ የሀሩራማ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ገረመው ጣሰው በወባ ፣ ትኩረት በሚሹ የሀሩራማ እና እንስሳት ነክ በሽታዎች ላይ ጥናትና ምርምሮችን እያካሄደ እና ሳይንሳዊ መረጃውችን እያመነጨ እንደሚገኝ ገልጸው በስድስት ወራቱ ከፍተኛ ተጽኖ ያላቸው 15 የጥናት ውጤቶች መታተማቸውን እንዲሁም በወባ ዘርፍ የወባ መከላከያና መቆጣጠር ስትራቴጂዎችን ለማጠናከር የሚያግዙ ምርምሮች በስፋት እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸው፣ 4ኛው ዙር የወባ ጠቅዋሚ ጥናት በሀገራቀፍ ደረጃ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል። ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎች ትኩረት ተሰጥቶ የወባ መከላከልና መቆጣጠር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የተላላፊ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክተር ዶ/ር ገመቹ ታደሰ በበኩላቸው፣ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ጥናቶች በስፋት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው እነዚህ ጥናቶች የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመቀነስ፣ የቅድመ መከላከል አገልግሎቶችን ለማጠናከር እና የመቆጣጠር ስርአቶችን ውጤታማ ለማድረግ ያተኮሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ለአብነትም ኤች አ ቪ እና አባላዘር በሽታውች በገጠርና በከተማ ያለውን ስርጭትና ጫና ፣ ቲቢ ፣ ፈንገስ ፣ የበሽታዎች መንስኤዎችና ቅኝት (Surveillance) ጥናቶች ፣ የክትባት ሽፋንና ተጽዕኖ ጥናቶች ፣ የተላላፊ በሽታዎች የምርመራ ዘዴዎችን ለማሻሻል የሚደረጉ ጥናቶች፣ የመድሀኒት ተጠቃሚነትና የመድሀኒት ብግርነት (Drug Resistance) ጥናቶች፣እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ትብብርና መደጋገፍም እየጎለበተ መምጣቱን ገልጸዋል:
በግምገማው የኢንስቲትዩቱ የምርምር ዘርፍ አመራሮች ፣ የአስተዳደር ዘርፍ ሀላፊዎች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
በመጨረሻም በስድስት ወራት የታዩ መልካም አፈጻጸሞችን በማስቀጠል የተለዩ ተግዳሮቶች ላይ በትኩረት እንዲሰራ የዘርፉ ሀላፊ እና የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የስራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን መልካም አፈጻጸም ለነበራቸውም እውቅና በመስጠት መድረኩ ተጠናቅቃል::