የኢንስቲትዩቱ የሥርዓተ ጤና ምርምር ዳይሬክቶሬት የ2019 ውጤት ተኮር ስትራቴጂካዊ ዕቅዱን አጸደቀ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥርአተ ጤና ምርምር ዳይሬክቶሬት በቢሾፍቱ ከተማ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን በመገምገም የ2019 ዓ.ም. ውጤት ተኮር ስትራቴጂካዊ አቅጣጫና ዓመታዊ ኦፕሬሽናል እቅዱን ሲያፀድቅ ፣ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ፣ “ከምርምር ወደ ውሳኔ፣ ከውሳኔ ወደ ተሻለ የጤና አገልግሎት” ሊያራምድ የሚችል ፣ጠንካራ የጤና ስርዓት የሚገነባው በጠንካራ ምርምር ነው” በማለት ምርምር በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ውሳኔንና የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የምርምር ጥራትን ማጠናከር፣ የምርምር ውጤቶችን ወደ ፖሊሲና አገልግሎት ማሸጋገር፣ የተቋማት ትብብርን ማሳደግ፣ የሀብት አጠቃቀምን ማሻሻል እና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የውሳኔ አሰጣጥን ማጠናከር ለ2019 በጀት ዓመት ቁልፍ የትኩረት መስኮች አድርገው እንዲሰሩባቸውም የሥራ አመራር ሰጥተዋል።
የሥርአተ ጤና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አደራጀው መኮንን በበኩላቸው፣ሀገር አቀፍ ጥናቶችን አለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቀ እና የሕብረተሰቡን ጤንነት በሚያሻሽል መልኩ በመስራት ውጤት ተኮር የሆነ የጤና ስርአት ለመገንባት አስቻይ ስራዎችን እየሰራን ነው ብለዋል።
ሀገራዊ ምርምሮች ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ ጥራት መከናወን እና ውጤቶቻቸው ወደ ፖሊሲና ተግባር መሸጋገር እንዳለባቸው በመጥቀስ ዳይሬክቶሬቱ የምርምር ግኝቶች ለውሳኔ አሰጣጥ የሚያገለግሉ የፖሊሲ አማራጮችን በማመንጨት ሰፋፊ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በዕውቀት ሽግግር፣ በጤና አገልግሎት፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣ በበሽታ ጫና እና ኢኮኖሚያዊ ምዘና፣ እንዲሁም በሥነ-ተዋልዶ ጤና ዙሪያ የተገኙ የምርምር ግኝቶች በየዲቪዥኑ ቀርበው ለቀጣዩ የ2019 ዓ.ም ስትራቴጂካዊ እቅድ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የውሳኔ አሰጣጥን በማጠናከር፣ የምርምር ውጤቶች በፖሊሲና በጤና አገልግሎት ላይ ተጨባጭ ተፅዕኖ እንዲፈጥሩ እና ለኢትዮጵያ ጠንካራ የጤና ስርዓት ግንባታ መሠረት የሚሆን ሥራ ለመስራት መታቀዱ ተገልጿል።
“ከምርምር ወደ ውሳኔ፤ ከውሳኔ ወደ ተሻለ የጤና አገልግሎት” የሚለው ፅንስሀሳብ ምርምር ውጤቶችን ወደ ፖሊሲና ወደ ተጨባጭ የጤና አገልግሎት በመቀየር ጠንካራ፣ ፍትሃዊና ውጤታማ የጤና ስርዓት ለመገንባት ወሳኝ መሠረት እንደሚጥሉ ይታመናል።