የጅጅጋው ሪፈረንስ እና የሆስፒታል ማዕከላዊ ላቦራቶሪዎች በይፋ ተመረቁ

የሶማሌ ክልል ብሄራዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ፣ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን የጅጅጋ ክልል ሪፈረንስ ላቦራቶሪን፤ የሼክ ሃሰን ያባሬ ሆስፒታል ማዕከላዊ ላቦራቶሪ መመረቃቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያስረዳል::
በምረቃ ስነስርአቱ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ እንደገለጹት በመርሃግብሩ የተመረቀው የጅጅጋ ክልል ሪፈረንስ ላቦራቶሪ ከዚህ ቀደም ከሚሰጠው መደበኛ የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎት በተጨማሪ በተጠናከረ ሁኔታ አድቫንስድ የሞሎኪዩላር/ PCR ምርመራ፣ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ሰርቪላንስ-ላቦራቶሪ፣ ማይክሮ ባዮሎጂ፣ ማይኮሎጂ ምረመራዎችን ለማካሄድ የሚያስችል ይሆናል፡፡
ሚንስትሯ አክለውም እንደተናገሩት ጤና ሚኒስቴር ዘመኑ የደረሰበትን የላቦራቶሪ ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር በማስገባት እና በማስፋፋት እንዲሁም የሰው ኃይል ልማት ላይ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት አድረጎ በመሥራት የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎቶች ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱ ተደራሽ እንዲሆን እስትራቴጂ ነድፎና ለዚህም መሳካት ተገቢውን አመራር እና ክትትል እያከናወነ ይገኛል፡፡
የሶማሌ ክልልም ለዘርፉ እየሰጠ ያለውን ከፍትኛ ትኩረት እንዲሁም ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል የሶማሌ ክልል ብሄራዊ መንግስት ፕሬዘዳንት ክቡር አቶ ሙስጠፌን፤ የክልሉን አመራር፤ የጤና ባለሙያዎቻችን እንዲሁም ለሶማሌ ክልል ህዝብ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና አንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ እንዳሉት ይህ ላቦራቶሪ ከዚህ ቀደም በኢንስቲትዩቱ አስተባባሪነት ተገንብተው ስራ እንደጀመሩት ላቦራቶሪዎች የላቀ ቴክኖሎጂ እና ከፍተኛ ብቃት ያለው በመሆኑ ለማህበረሰቡም ብሎም ለዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረው ሲሆን ወቅቱን የጠበቀ እና ትክክለኛ መረጃ ከመለዋወጥ አንጻርም ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሮ አብደላ በበኩላቸው ለዝግጅት ክፍላችን ባደረሱን መረጃ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የክልሎችን አቅም ለማጐልበት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ በሁሉም ክልሎች የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶችን እና የክልል ላቦራቶሪዎችን በመገንባት እና አስፈላጊ ግብዓቶችን በሟሟላት ከሁሉም ክልሎች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸው ከዚህ በፊት በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደር ከነበሩት የክልል ላቦራቶሪዎች በተጨማሪ መንግስት አስፈላጊውን ሀብት በመመደብ ከግሎባል ፈንድና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር 13 ላቦራቶሪዎች የገነባ ሲሆን፣ ይህም ዛሬ የተመረቀው የጂጂጋ ክልል ሪፈረንስ ላቦራቶሪ የዚህ ፐሮጀክት አንድ አካል መሆኑን ገልጸዋል::