የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በሶማሌ ከልል፣ ጅግጅጋ በይፋ ተጀመረ

ሀገር አቀፉ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሃ ግብርን ዛሬ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ፣ የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጃ ዱጉማ፣ የኢትዮጰያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ፣ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ፣ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የጤናው ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት አስጀምረዋል።
በክልሉ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ህፃናት ይከተባሉ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ በክልሉ የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል በተከናወነው ስራ አመርቂ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን ለዚህም ውጤት በማህበረሰቡ ላይ ይስተዋል የነበረውን የተሳሳተ አመለካከትን መቅረፍ በመቻሉ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የጤና ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጃ ፖሊዮን ከሀገር ለማጥፋት በተለያዩ ፕሮግራሞች ክትባቶች ሲሰጡ ከመቆየታቸውም በተጨማሪ ከአጎራባች ሀገሮች ጋር በዚህ ረገድ የበሽታ ቅኝትን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ዶ/ር መሳይ በበኩላቸው የፖሊዮ በሽታን ጨርሶ ለማጥፋት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንና በሀገር አቀፍ ደረጃ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ወደ 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናትም የልጅነት ልምሻ(#ፖሊዮ) ክትባትን እንደሚከተቡ አስረድተዋል።
እንደ ኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ ገለጻ ከዛሬ ጀምሮ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና በዘጠኝ ክልሎች ሀገር አቀፍ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ይካሄዳል። በዚሁ የክትባት ዘመቻም 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ህፃናት የሚከተቡ ሲሆን ክትባቱ ከቤት ለቤት አገልግሎት በተጨማሪ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በህፃናት ማቆያና በጤና ተቋማትና በሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት በነፃ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።
ለዚህ የክትባት ዘመቻም በርካታ ባለሙያዎች ክትባቱን መስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን ከመድረኩ ለመረዳት ተችሏል።