ኢትዮጵያ 7ኛውን የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለማስተናገድ ዝግጅቷን ያጠናቀቀች መሆኗ ተገለጸ

ኢትዮጵያ 7ኛውን የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከጥቅምት 24 እስከ 26 ቀን 2019 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ለማካሄድ ያላትን ዝግጁነት ዛሬ ጥቅምት 20 / 2019 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠች።
የጋዜጣዊ መግለጫ ዋና ዓለማ ኢትዮጵያ የሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የድንገተኛ ጤና ምላሽ አቅምን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን እንዲሁም የሥራ ልምዷን ለዓለም ለማካፈል፣ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ለመቅሰምና በክልላዊና ዓለም አቀፋዊ የጤና ድንገተኛ ዝግጁነት ላይ ያላትን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ከጥቅምት 24 እስከ 26 / 2019 ዓ.ም በምታደርገው 7ኛ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ለጋዜጠኞች ግንዛቤ ለመፍጠር ነው።

ወ/ሮ ነኢማ ዜይኑ በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና ደንገተኛ አደጋ ዝግጁነት ደይክቶሬት ዳይሬክተር በጋዜጣዊ መግለጫው እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያ ከአንድ ወር በፊት በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀዳሚ የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች አስተዳደር በመሆን እውቅና ማግኘቷ ይታወሳል። ኢትዮጵያ ይህን 7ኛውን ጉባኤ በማስተናገድም በአፍሪካ ይህን ዓለም አቀፍ ዝግጅት የምታስተናግድ የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗን ጠቁመዋል።
በበሽታ ወረርሽኞች፣ በተፈጥሮ አደጋዎችና በሌሎች ድንገተኛ ቀውሶች ወቅት የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ በቂ ሥልጠና፣ መሣሪያና ቅንጅት ያላቸው የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው እና የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች ኢኒሼቲቭም ሀገራት ዓለም አቀፍ የሥራ መስፈርቶችን እንዲከተሉ፣ የምላሽ አቅማቸውን እንዲያጠናክሩና ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ቀውሶችን በጋራ እንዲቋቋሙ እንደሚያግዝ ወ/ሮ ነኢማ አያይዘው አብራርተዋል።
ወ/ሮ ነኢማ ጨምረው ኢትዮጵያ የድንገተኛ ሕክምና ምላሽ አቅሟን ለማጠናከር ባለፉት ዓመታት ተከታታይ እርምጃዎችን መውሰዷን በመግለጫው ያመለከተቱ ሲሆን በ2018 ዓ.ም. የአደጋ ሕክምና ድጋፍ ቡድን (Disaster Medical Assistance Team — DMAT) ተቋቁሞ፣ በመስከረም 2019 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ የድንገተኛ ሕክምና ቡድን የዓለም ጤና ድርጅትን የማረጋገጫ ሂደት በማለፍ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱን ተናግረዋል ።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች የ2025–2030 ስትራቴጂክ ዕቅድ የአመራርና አስተዳደር ሥርዓትን፣ ቅንጅትና ትብብርን፣ የመረጃና ዕውቀት አያያዝን፣ የሰው ኃይል ልማትን፣ የሎጂስቲክስ አቅምንና የጥራት ማረጋገጫን እንደ ዋና የትኩረት መስኮች መያዙን ፣ ዕቅዱ በክልል ደረጃ የድንገተኛ ሕክምና ምላሽ አቅምን በማስፋፋት፣ የአደጋ ድጋፍ ለተጎጂ ማኅበረሰቦች በፍጥነት እንዲደርስ ለማስቻል ያለመ መሆኑን በነበረው መግለጫ በሰፊው ተብራርቷል ።
የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የድንገተኛ ጊዜ መርሃ ግብር ኃላፊ ፕሮፌሰር ቴሪኖ ባልዴ በበኩላቸው የሚካሄደውን ጉባኤ አስመልክቶ እንደ ገለጹት ከ100 በላይ አገራትን የወከሉ ከ800 በላይ ተሳታፊዎች በጉባኤው የሚሳተፉ መሆናቸውን፣ የድንገተኛ ሕክምና ምላሽ ሥርዓቶችን ለማጠናከር፣ የአገራትን የዝግጁነት አቅም ለማሳደግና በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና ደህንነትን ለማረጋገጥ ያላቸውን ዝግጁነት አስመልክቶ በጉባኤው በጥልቀት ውይይትና የልምድ ልውውጥ የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዓለም አቀፉ ስብሰባ አንድ ቀን በፊት፣ ጥቅምት 23 ቀን 2019 ዓ.ም. ሰፊ የሙከራ ልምምድ (Simulation Exercise — SIMEX) እንደሚካሄድ፣ ልምምዱ የሀገሪቱን የቅንጅትና የሥራ አፈጻጸም ሥርዓቶች በተግባር ለመፈተሽ፣ ክፍተቶችን አስቀድሞ ለመለየትና የዝግጁነት አቅምን ለማጠናከር እንደሚያግዝ በመግለጫው ተገልጿል።