የመካከለኛ የፊልድ ኤፒዲሞሎጂ የአማካሪዎች ስልጠና ተጀመረ

ከኢጋድ (IGAD)፣ ከምስራቅ፣ ማዕከላዊና ምሥራቅ አፍሪካ የጤና ማህበረሰብ (ECSAHC)፣ ከአፍሪካ ፊልድ ኤፒዲሞሎጂ ኔትዎርክ (AFENET) እንዲሁም ከአሜሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር (US-CDC) ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የመካከለኛ የፊልድ ኤፒዲሞሎጂ የስልጠና (I-FELTP) አማካሪዎች ስልጠና በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ተጀመረ።
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢትዮጰያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የፊልድ ኤፒዲሞሎጂ ስልጠና ፕሮግራም ክህሎትን መሠረት ያደረገ በመሆኑ የኤፒዲምሎጂ እና የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች የቅኝትና ምላሽ ስርዓቱን አቅም የሚገነባ በመሆኑ በኢትዮዽያ ተፅእኖ ከሚፈጥሩ ፕሮግራሞች አንዱ ነው።
ዶ/ር መሳይ አያይዘውም የዚህን ፕሮግራም መሠረታዊ ስልጠና ያጠናቀቁ ከሌሎች የጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን የተለያዩ ተላላፊም ሆነ የማይተላለፉ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ላይ በመሳተፍ ከስልጠናው ያገኙትን ብቃት ያስመሰከሩ ሲሆን በቀጣይም ኢንስቲትዩቱ ለፕሮግራሙ መሳካት በሙሉ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
የFELTP ስልጠና በኢትዮጵያ ከተጀመረ እ.ኤ.አ 2009 ጀምሮ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እና በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እየተመራ በርካታ ባለሙያዎችን አሰልጥኗል። እነዚህ ባለሙያዎች በክልሎች እና ወረዳዎች በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች በመስራት ላይ የሚገኙ ሲሆን ከሀገራቸው አልፈው እንደ አስፈላጊነቱም ለጐረቤት ሀገራትም ያግዛሉ።
በዚህ የI-FELTP የስልጠና የአማካሪዎች ስልጠና ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የ #IGAD የጤና እና ማህበራዊ ልማት ዳይሬክተር፣ የ #USCDC፣ የ #AFENET እና የ #ECSAHC አመራሮች በስነ ስርዓቱ ላይ የበኩላቸውን መልዕክቶች አስተላልፈዋል። በተጨማሪም ከብሩንዲ፣ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጐ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሳዎ ቴሜና ፕሪንሲፔ፣ ዛምብያ እና ማላዊ የመጡ እንግዶች በፕሮግራሙ ላይ ተሳትፈዋል።