10ኛው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ጉባዔ በሐዋሳ እየተካሄደ ነው

“የማይበገር የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስርዓት ለብሔራዊ ጤና ደህንነት” በሚል መሪ ቃል 10ኛው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ጉባዔ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እና የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች፣ የኢትዮጵያ አደጋና ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም፣ የፌደራል ፖሊስ ጤና መምሪያ ኃላፊ፣ የክልል ጤና ቢሮ እና የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊዎች እና የአጋር ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት በሐዋሳ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አየለ ተሾመ በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለፁት ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር እንዲሁም ክስተቶቹ የሚያስከትሉትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጫና መቀነስ እንዲቻል ከላይ እስከታች ያለው የጤናው ዘርፍ መዋቅር የወቅቱን ተጫባጭ ሁኔታ የሚመጥን ዝግጅት እና አቅም ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በሀገራችን ጤንነቱ የተጠበቀ እና አምራች ዜጋ ለመፍጠርና ለሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች የማይበገር የጤና ስርዓት ለመፍጠር ለሚናደርገው አገራዊ ዕቅድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራት እና ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው መድረኩ ዘርፈ-ብዙ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከል ዕቅዶችና ተግባራት በሁሉም መዋቅሮች ውስጥ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ የተለያዩ ስልቶች የሚቀየሱበትና የጋራ መግባባት ላይ የሚደረስበት መድረክ መሆኑን በማብራራት ከባለፈው ጉባኤ ወዲህ የተከናወኑ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስራዎችን አፈጻጸም በጋራ የምንገመግምበት፣ አዲስ የተከሰቱ እና በድጋሚ የሚከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች እና የጤና ክስተቶች መከላከልና ቁጥጥር ተግዳሮቶች ላይ የጋራ መፍትሔዎችን የምናፈላልግበት መድረክ ነው በማለት ገልጸው እየተተገበሩ ያሉ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከልና ቁጥጥር ቅንጅታዊ ስራዎች የህብረተሰባችንን ጤና ለማሻሻል የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል::
ይህ ለ10ኛ ጊዜ የምናካሂደው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ጉባዔ ልምዶቻችንን እና እውቀቶታችንን የምንለዋወጥበት እንዲሁም አንዳችን ከአንዳችን የምንማርበት ሲሆን ያለፉት ስኬቶቻችንን እና ክፍተቶቻችንን የምንገመግምበትና የምንለይበት የወደፊት አቅጣጫዎቻችንን ደግሞ በጋራ የምንቀይስበት እና አብረን በትብብር ለመስራት ቃል የምንገባበት መድረክ ነው በማለት የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ ናቸው።
በተጨማሪም በጉባዔው ማስጀመሪያ ዕለት የኢትዮጵያ አደጋና ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም “የቤተሰብ ኃላፊነትና የማሕበረሰብ አጋርነት ለሁሉም ዓይነት አደጋዎች አይበገሬነት” በሚል ርዕሰ የተዘጋጀ ፅሁፍ ያቀርቡ ሲሆን የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ስላማዊት መንገሻ እንዲሁም የሲዳማ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡
ጉባዔው እስከ የካቲት 2/2017 የሚቀጥል ሲሆን በመጀመሪያው ቀንም የጉባዔው ተሳታፊዎች በመስክ ምልከታ በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ሚሊኒየም ጤና አጠባበቅ ጣቢያ እና የሲዳማ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እየተሰሩ ያሉ የሕብረተሰብ ጤና ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡