3ኛው ዙር የAVoHC-SURGE ሰልጣኖች ተመረቁ

ከተለያዩ የሴክተሮች ተውጣጥተው ሶስተኛውን ዙር የAfrican Volunteers Health Corps Strengthening and Utilizing Response Groups for Emergencies (AVoHC-SURGE) ስልጠናን ያጠናቀቁ 114 ባለሙያዎች የካቲት 8/2017 ዓ.ም የዕውቅና የምስክር ወረቀታቸውን ተቀብለዋል።
ሰልጣኞቹ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከክልሎች፣ ከሆስፒታሎችና ከሴክተር መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ ናቸው።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር የዝግጁነት፣ የቅኝት እንዲሁም አደጋዎች ሲከስቱ ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅማችንን ከማጠናከር ረገድ ሰፊና ዉጤታማ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ በአጭርና መካከለኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ልዩ ልዩ ሙያ ያላቸው ከፍተኛ ባለሙያዎች መረጃን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመያዝና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት ለተልዕኮ ዝግጁ በማድረግ እየሰራ እንደሆነና የሚከሰቱ የህብረተሰብ ጤና ስጋቶችን ለመቀነስ እና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እየተደረገ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥረት ባለሙያዎቹ ይበልጥ እንደሚያጠናክሩት ገልጸዋል ::
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው ለዕውቅና የበቁት ባለሙያዎች በአጠቃላይ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች የሚፈጥሩትን አሉታዊ ተፅእኖች ከመከላከል ብሎም ከመቀነስ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
የአሁኑን ተመራቂዎች ጨምሮ እስካሁን 304 ባለሙያዎች መመረቃቸውንና በፕሮግራሙ ከተያዘው አጠቃላይ 700 ባለሙያዎችን ለማሰልጠንና ለማስመረቅ ከተያዘው እቅድ ወደ 44 በመቶ የሚጠጋ ሲሆን በቀጣይም በተለያዩ ዙሮች ስልጠናው የሚቀጥል መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአለም የጤና ድርጅት በኢትዮጵያ ዳይሬክተርን በመወከል አቶ አስቻለው አባይነህ ናቸው።
የጦር ኃይሎች ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አዛዥ እና የፌደራል ፖሊስ ጤና መምሪያ ኃላፊ ተወካዮች ስልጠናው ለድንገተኛ የጤና አደጋዎች መከላከል፣ መቆጣጠር እንዲሁም ምላሽ በመስጠት በኩል ያለውን ጠቀሜታ እንዲሁም ተቋማቱ በይበልጥ ተቀናጅተው እንዲሰሩ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።