4ኛው ዙር የወባ ጠቋሚ ጥናት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በቢሾፍቱ ተካሂዷል።

የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሚያካሂደው አራተኛው ዙር የወባ ጠቋሚ ጥናት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በቢሾፍቱ ዕየተካሄደ ሲሆን በማስጀመሪያ መርሀግብሩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ እንዳሉት የበሽታ መከላከልን መሰረት ባደረገ ስራ የኤች አይ ቪ፣ ወባና ቲቢ በሽታ የስርጭት ምጣኔ ላይ መቀነስ ታይቷል።
ሆኖም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች በአንዳንድ አካባቢዎች የወባ ምጣኔ ከፍ ማለቱን ተከትሎ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል። የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ፣ የአልጋ አጎበር ስርጭትና የፀረ-ወባ ኬሚካል ርጭት ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን ገልፀዋል።
በዚህም የወባ ስርጭት ምጣኔ አምና ከነበረበት ጋር ሲነጻጸር 40 በመቶ መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት። የወባ ከፍተኛ ምጣኔ ባለባቸው አካባቢዎች ትኩረት ተደርጎ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የወባ ጠቋሚ ጥናት በሁሉም ክልሎች እንደሚካሄድ ተናግረዋል። ጥናቱ እስካሁን የወባ በሽታን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ውጤታማነት የሚገመግምና ለቀጣይ ዓመታት የሚሰራባቸውን ስትራቴጂዎችና የመንግስት እቅድ የሚያመላክት የመረጃ ምንጭ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም የምርምር ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። አራተኛው ዙር የወባ ጠቋሚ ጥናት ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራት ጥንካሬና ድክመትን ለመለየትና ቀጣይ አቅጣጫን ለማሳየት የሚረዳ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ ዳሰሳውን ለማድረግ በሳይንሳዊ ዘዴ በተመረጡ ሰዎች ላይ የወባን የተጋላጭነት ልኬት ማወቅ፣ በቤተሰብ ደረጃ በኬሚካል የተነከሩ የአልጋ አጎበሮችን የባላቤትነትና የአጠቃቀም ልየታ፣ በአባወራ/እማወራ ደረጃ የወባ በሽታን አስመልክቶ ያለውን የእውቀት የአመለካከት እና ገቢራዊ ክንዋኔን መፈተሽ፣ ዕድሜያቸው ከ6-59 ወራት በሆኑ ህፃናት ላይ የደም ማነስ ስርጭትን መለየት ከጥናቱ ዓላማዎች በጥቂቱ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የኢንስቲትዩቱ የወባ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ገረመዉ ጣሰዉ በበኩላቸው ከፍተኛ የወባ ስርጭት ምጣኔ ባለባቸው አካባቢዎች ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ያለው የወባ መከላከልና መቆጣጠር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶ/ር አዱኛ ወዬሳ በበኩላቸው ጥናቱ ቤት ለቤት የሚካሄድና በ268 መረጃ ሰብሳቢ ባለሙያዎች የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመው ከ14ሺህ በላይ አባወራዎችና እማወራዎች የሚሳተፉበት ጥናቱ ዓለም አቀፋዊ መስፈርቶችን የተከተለ መሆኑንም አስረድተዋል።
ዶ/ር ሕይወት ሰለሞን በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚና የዚህ ጥናት ስትራቴጂ አማካሪዎች ሰብሳቢ እንዲሁም የAHRI እና የኢንስቲትዩቱ አመራሮች በስነስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።