በመላው አገሪቱ ያለውን የተጓዦችና የድንበር ጤና ቁጥጥር አስመልክቶ የምክክር መድረክ ተካሄደ

የኢንስቲትዩቱ የተጓዦችና የድንበር ጤና ዳይሬክቶሬት ተላላፊ የሆኑ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ በሽታዎችን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር በመላው አገሪቱ የየብስ እና የአየር መውጫና መግቢያ ኬላዎች ላይ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የ6 ወራት የቁጥጥር ስራዎችን አስመልክቶ የካቲት 24 እና 25/2017 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡
አቶ ታምሩ ታደሰ የተጓዦችና የድንበር ጤና ዳይሬክቶሬት ባለሙያ የምክክር መድረኩን ዋና ዓላማ አስመልክቶ እንደገለጹት በመላው የአገሪቱ የመግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ በበጀት ዓመቱ የተሰሩ ውጤታማ ስራዎች እና የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት እና የጋራ የስራ መርሃ ግብር በማውጣት የተላላፊ በሽታዎችን በፍጥነትና በጥራት የመቆጣጠር እና ምላሽ የመስጠት ተግባርን ለማከናወን ብሎም የባለድርሻ አካላትን ቅንጅትና ትብብር የበለጠ ለማጠንከር የተካሄደ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአገሪቱ በየብስና በአየር መውጫ እንዲሁም መግቢያ ኬላዎች ላይ የድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር እና የተጓዦች ጤና አገልግሎትን አስመልክቶ የተከናወኑ የተለያዩ የስራ አፈጻጸም ሪፖርቶች በመድረኩ ቀርበው ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች፣ የነበሩ ክፍተቶች በተለይም ማነቆ የነገሩ ተግዳሮቶች የመለየት ስራ ከመሰራታቸውም በላይ በነበሩት ክፍተቶች ላይ የቀጣይ የስራ መረሃ ግብር /Action plan/ በማውጣት የምክክር መድረኩ ተጠናቋል፡፡
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የመተማ መግቢያና መውጫ ባለድርሻ ጽ/ቤቶች፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ እና ባለድርሻ መስሪያ ቤቶች፣ በኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት አስተዳደር የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ቅ/ጽ/ቤት፣ ባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ቅ/ጽ/ቤት እና የመሳሰሉት ባላድርሻ መስሪያ ቤት ተወካዮች በምክክር መድረኩ ተሳትፈዋል፡፡
እንደሚታወሰው ባለፈው ሳምንት የካቲት 21/2017 ዓ.ም ዳይሬክቶሬቱ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዉስጥ የሚደረገውን የድንበር ተሻጋሪ የተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥርና የተጓዦች ጤና አገልግሎት አፈጻጸምን በተመለከተ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ስጋትና ተግባቦት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በቢሸፍቱ ከተማ አካሂዷል። በዚህ መድረክም የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ መከላከልና መቆጣጠር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርፖርት ክሊኒክ እንዲሁም ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር የሚሰሩ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ኢንተርናሽናል ሆቴሎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።