ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የሚያገለግል ወጥ የጤና መረጃ ቋትና የዕውቀት ማዕከል ይፋ ሆነ

የሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት የጤና ሁኔታ በተመሳሳይ መመዘኛ የሚያሳዩት “የአፍሪካ የጤና አትላስ (Africa Health Atlas)” እና “የአፍሪካ የጤና ዕውቀት ማዕከል (Africa Health Knowledge Hub)” በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና ዓለም አቀፍ ጉባኤ (#CPHIA2026) ላይ በይፋ ተመርቀዋል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ይህንን አህጉራዊ ፋይዳ ያለው መድረክ ከአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) እንዲሁም ከጤና መለኪያዎችና ግምገማ ተቋም (IHME) ጋር በመተባበር በይፋ አስጀምረዋል።
ዶ/ር ጌታቸው እንደገለጹት በ2023 ዓለም አቀፍ የበሽታዎች ጫና ጥናት (GBD 2023) ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀው ይህ አትላስ፣ ለ54ቱ የአፍሪካ ሀገራት እና ለአፍሪካ ኅብረት አንድ ዓይነት የጤና አመላካቾችን ያቀርባል። በተጨማሪም ለኢትዮጵያ፣ ለኬንያ፣ ለናይጄሪያ እና ለደቡብ አፍሪካ እስከ ታችኛው አስተዳደራዊ እርከን (Subnational) ድረስ የወረደ ዝርዝር መረጃን ያካትታል።
ከጥናቱ የተገኙ ቁልፍ ግኝቶች መካከል በአፍሪካ አማካይ የመኖር ዕድሜ ጣሪያ (Life expectancy) 65.3 ዓመት ሲሆን፣ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ 55.0 ዓመት እንዲሁም በኮሞሮስ 76.3 ዓመት ሆኖ ተመዝግቧል። ይህም በሀገራቱ መካከል የ21.3 ዓመት ሰፊ ልዩነት መኖሩን ያሳያል።
እንዲሁም ድርብ የበሽታ ጫናን በተመለከተ እ.ኤ.አ. ከ1990 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች (NCDs) ምክንያት የሚከሰት ሞት ከ25.2 በመቶ ወደ 44.9 በመቶ አሻቅቧል። በአንጻሩ በተላላፊ በሽታዎች፣ በእናቶችና ጨቅላ ሕፃናት ጤና እንዲሁም በሥርዓተ-ምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰት ሞት ከ66.7 በመቶ ወደ 44.2 በመቶ ዝቅ ብሏል።
በተያያዘ መልኩም በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ጥናቱ እንደሚያሳየው ፖሊሲ አውጪዎች ከአህጉር አቀፍ ደረጃ እስከ ወረዳ ድረስ ያለውን የጤና ዕድገት ለመገምገምና ከፍተኛ የበሽታ ጫና ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ኢንቨስትመንትን ለማተኮር ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
በዚህ ስራ ላይ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደርና ትንተና ማዕከል (NDMC)፣ ልምዱን በማካፈልና ይህንን አህጉራዊ ተነሳሽነት ከIHME እና ከአፍሪካ ሲዲሲ ጋር በመደገፍ ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
“የአፍሪካ የጤና ሉዓላዊነት የሚጀምረው የራሳችንን አኃዞችና መረጃዎች በትክክል ከማወቅ ነው” ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በአዲስ አበባ በተካሄደው በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ ለተገኙ ባለድርሻ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።