የ2019 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንትን በኢንስቲትዩቱ ተከበረ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2019 ዓ.ምን ዓለም አቀፍ የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ (Antimicrobial Resistance /AMR/) ግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንትን “አንድ ጤና፣ አንድ ተግባር፦ የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች ብግርነትን አሁን እንከላከል!” በሚል መሪ ቃል አከበረ።

በመርሐ ግብሩ የተለያዩ የጤና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የመድኃኒት ቁጥጥር አካላትና አጋር ድርጅቶች ተሳትፈዋል። ተሳታፊዎቹ በሰው፣ በእንስሳትና በአካባቢ ጤና ዘርፎች የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች ብግርነትን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ገምግመው፣ የቅኝት መረጃዎችን ወደ ተግባራዊ እርምጃ ለመቀየር የተቀናጀ የዘርፈ ብዙ ትብብር አስፈላጊነትን አንስተዋል።
የኢንስቲትዩቱ የተላላፊ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ገመቹ ታደሰ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች ብግርነትን መከላከል በዓመት አንድ ጊዜ በሚካሄድ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብር ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ የሚቀጥል ቁርጠኝነትና ተግባራዊ ርብርብ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።
ዶ/ር ገመቹ የችግሩን ዓለም አቀፋዊ የጤናና የኢኮኖሚ ተጽዕኖ፣ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪና በጤና ተቋማት ውስጥ የሚከሰት የመተላለፍ ሥጋትን በማንሳት፣ ሳይንሳዊ ዕውቀትን ወደ ተግባራዊ አፈጻጸም መቀየር የጤና ባለሙያዎች፣ የተቋማትና የሁሉም ዜጎች የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አጽንኦት በመስጠት አስረድተዋል።
በተጨማሪም በሆስፒታሎችና በክልል ላቦራቶሪዎች እየታዩ ያሉ አበረታች ለውጦችን በማድነቅ፣ በመድኃኒት ብግርነት ምክንያት የሚከሰቱ ሞቶችን ለመቀነስና የታካሚዎችን የጤና ደህንነትን ለመጠበቅ የተቀናጀ አሠራር፣ የመረጃ ጥራትና ጠንካራ አመራር ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በእንስሳት ነክ በሽታዎችና በፀረ-ወባ መድኃኒቶች ብግርነት ቅኝት ሥርዓቶች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የኢንስቲትዩቱ የወባና ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ገረመው ጣሰው፣ ኢንስቲትዩቱ የላቦራቶሪ ማስረጃዎችን በማመንጨት፣ የበሽታ ቅኝትን በመደገፍና ፖሊሲዎችን በሚደግፉ መረጃዎች በማቅረብ ረገድ ማዕከላዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸው የፀረ-ተህዋሲያንና የፀረ-ወባ መድኃኒቶችን ውጤታማነት መከታተል፣ ለጤና ሚኒስቴር ተገቢውን መድኃኒት ለመምረጥና የሕክምና መመሪያዎችን በወቅቱ ለማሻሻል የሚያስችል ወሳኝ መረጃ እንደሚያቀርብም አብራርተዋል።
ዶ/ር ገረመው አያይዘውም የሰው፣ የእንስሳትና የአካባቢ ጤና በጥብቅ የተሳሰሩ መሆናቸውን በመግለፅ ፣ በእንስሳት ላይ ተገቢ ያልሆነ የመድኃኒት አጠቃቀም፣ የተበከለ ውኃና የምግብ ሰንሰለት በሰው ጤና ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ጠቁመዋል። ውጤታማ መከላከል ለማምጣትም በሐኪሞች፣ በእንስሳት ሐኪሞች፣ በላቦራቶሪ ሳይንቲስቶች፣ በአካባቢና በምግብ ደኅንነት ባለሙያዎች፣ በአርሶ አደሮችና በቁጥጥር አካላት መካከል ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
በዘርፉ ከፍተኛ ተመራማሪ እና የረጅም ጊዜ ልምድ ያካባቱት የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች አቶ ገብሬ አለባቸው የበዓሉን ዓላማ ያብራሩ ሲሆን ዶ/ር ነጋ አሳመነ በበኩላቸው የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች ብግርነት ቅኝት ሥርዓት አተገባበርና ተግዳሮቶችን በተመለከተ ገለጻ አድርገው የእለቱ መድረክን የመዝጊያ ንግግር አድርገዋል።