በምርምር የተገኙ ማስረጃዎች ለሕብረተሰብ ጤና ፖሊሲና ውሳኔ አሰጣጥ ወሳኝ ናቸው

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኖርዌይ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (NIPH) ጋር በመተባበር፣ ተመራማሪዎች የምርምር ውጤቶችን በሥርዓት የመተንተንና የመገምገም አቅማቸውን ለማጠናከር ብሎም በምርምር የተገኙ ማስረጃዎች ለሕብረተሰብ ጤና ፖሊሲና ውሳኔ አሰጣጥ በተሻለ ሁኔታ እንዲውሉ ለማገዝ ያለመ ነው።

በሁለቱ ኢንስቲትዩቶች የሁለትዮሽ (BIS 26) ትብብር ማዕቀፍ የሚካሄደው ይህ ሥልጠና፣ ከተለያዩ የኢንስቲትዩቱ የምርምር ክፍሎች የተውጣጡ ተመራማሪዎች ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን የመተንተን፣ የማዋሃድና ለሕዝብ ጤና ፖሊሲ ውሳኔዎች የሚያግዙ ግኝቶችን የማቅረብ አቅማቸውን ለማጠናከር ያለመ ነው።
ሥልጠናው በኖርዌይ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የማስረጃ ውህደት ባለሙያ በፕሮፌሰር ሪግሞር በርግ እየተመራ ሲሆን፣ ሥርዓታዊ ግምገማዎችን፣ የወሰን ግምገማዎችን (Scoping Reviews) እና ፈጣን ግምገማዎችን (Rapid Reviews) ይሸፍናል። በተጨማሪም የPICO ሂደትን የተከተለ የጥያቄ አቀራረብ፣ የመረጃ ማውጣት፣ የአድሏዊነት ስጋት ግምገማ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውን Grading of Recommendations Assessment, Development and Evaluation (GRADE) ማዕቀፍን በመጠቀም የማስረጃ ጥራትን መመዘን ስልቶች የሥልጠናው አካል ናቸው።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥርዓተ ጤና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አደራጀው መኮንን፣ ትብብሩ ተመራማሪዎች ጥብቅ የምርምር ዘዴን የተከተሉና ከፖሊሲ ውሳኔዎች ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ማስረጃዎች እንዲያመነጩ በማብቃት ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።
የኢንስቲትዩቱ እውቀት ትርጉምና ስርጭት ዲቪዥን ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ጌታቸው በበኩላቸው፣ በኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የምርምር ክፍሎች ለስልጠናው ባሳዩት ከፍተኛ ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ሥልጠናው በተከታታይ ዙሮችን ለማካሄድ እንደሚያስችል ጠቁመው፣ በቀጣዬቹ የሥልጠና ዙሮች የሚሳተፉ ተመራማሪዎችም የተጠናቀቁና በተግባር ሊውሉ የሚችሉ ሥርዓታዊ ግምገማዎችን እንደሚያዘጋጁ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የኖርዌይ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ትብብር በኢትዮጵያ የሳይንሳዊ ማስረጃዎች ወደ ፖሊሲና ተግባር የሚተላለፉበትን ሥርዓት ለማጠናከርና የሕብረተሰብ ጤና ፖሊሲዎች በጠንካራ ሳይንሳዊ ማስረጃ ላይ እንዲመሠረቱ ለማገዝ ያለመ ነው።