በጋምቤላ የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሄደ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የኮሌራ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ፣ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ፣ የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አቤል አሰፋ፣ የክልሉ የብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሸኔ አስቴን እንዲሁም የአጋር ድርጅቶች ኃላፊዎችና ተወካዮች በተገኙበት መጋቢት 20/2017 ዓ.ም በጋምቤላ ከተማ የኮሌራ ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሄደ፡፡

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ በመረሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት የኮሌራ በሽታ የማህበረሰቡ አደገኛ የጤና ችግር በመሆኑ በሽታውን ለመከላከል በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀው በተለይም በሽታውን ለመከላከል በዕለቱ ለተጀመረው የክትባት ዘመቻ ስኬታማነት በየደረጃ የሚገኙ የአመራር አካላት ህዝቡን በማስተባበር ጠንክረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንድገለጹት ደግሞ አሁን ላይ የኮሌራ በሽታ የማህበረሰቡ የጤና ስጋት እንዳይሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሀገራዊ እቅድ በማዘጋጀት ከአጋር ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ይህንንም ታሰቢ በማድረግ በጋምቤላ ክልል የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት እንዲሰጥ መደረጉን ጠቁመው ለስኬታማነቱ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማጠናክር ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ኢንስቲትዮቱ የተጠናከረ የቅኝትና የምርምር ስራዎች በማከናወን ድንገተኛ የጤና አደጋዎችንና ወረርሽኞች ለመከላከል በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረው በአሁኑ ወቅትም በጋምቤላ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችና የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት መስጠት ማስፈለጉን ተናግረዋል።
ይህ የክትባት ዘመቻ ከዛሬ ጀምሮ ለተክታታይ ሰባት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን እድሜያቸው ከአንድ ዓመት በላይ የሚገኙትን የህፃናትን ጨምሮ ከ990 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር አቤል አስታውቀዋል።
በዕለቱም የአለም የጤና ድርጅት ተወካይ ድርጅታቸው ያደረገውን የተለያዩ የሕክምና ግብዓቶች ድጋፍ ያስርከቡ ሲሆን በጋምቤላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችም ተጐብኝተዋል።