ከ800 በላይ ባለሙያዎችን ያፈራው የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ፕሮግራም የ15 ዓመታት ውጤቱን ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ፊልድ ኤፒዲሚዮሎጂና ላቦራቶሪ ሥልጠና ፕሮግራም (EFELTP) ከ2009 እስከ 2024 ያስመዘገበውን የ15 ዓመታት የስኬት ውጤትና ለጤና ስርዓቱ ያበረከተውን አስተዋጽኦ የግምገማ ውጤት ይፋ አደረገ።
የግምገማ ውጤቱ ይፋ የሆነው የአለም አቀፉ የፊልድ ኢፒዲሚዮሎጂ ቀን በሚታሰብበት ቀን በአዲስ አበባ በተካሄደው የEthiopian Field Epidemology and Laboratory Training Program (EFELTP-Advanced) የምርምር ግኝቶች ማጠቃለያ መድረክ ላይ ነው።

በመድረኩ የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ እንደገለጹት፣ EFELTP ባለፉት 15 ዓመታት ከ800 በላይ የሆኑ ባለሙያዎችን በማሰልጠን በአገሪቱ የሚከሰቱ የጤና ሥጋቶችንና የበሽታ ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጉልህ ሚና ተጫውቷል። በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የሰለጠኑ ባለሙያዎች በምላሽ ሥራዎች ላይ ያደረጉት ተሳትፎ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ደረጀ በቀጣይ የፕሮግራሙን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የሰው፣ የእንስሳትና የአካባቢ ጤናን በማቀናጀት የአንድ ጤና (One Health) አቀራረብን ማጠናከር፣ የላቦራቶሪና የፊልድ ኤፒዲሚዮሎጂ መረብን ማስፋፋት፣ ተጨማሪ እና ዘላቂ የአገር ውስጥና የክልል የበጀት ምንጮችን መፍጠር፣ የዲጂታል ጤናና የወረርሽኝ መረጃ ሥርዓትን ማዘመን እና የባለሙያዎችን የሥራ እድገትና ቆይታ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ በበኩላቸው፣ የፕሮግራሙ ግምገማ የተካሄደው በኢትዮጵያ የሕብረተሰበ ጤና ኢንስቲትዩት መሪነት ሲሆን፣ ፕሮግራሙ በ8 ዩኒቨርሲቲዎችና በበተለያዩ ክልሎች በሚገኙ 42 የመስክ ማዕከላት ከ800 በላይ ባለሙያዎችን ማሰልጠኑን ገልጸዋል። ባለሙያዎቹም ኮቪድ-19ን ጨምሮ በሀገራችን በተከሰቱ የተለያዩ የበሽታ ወረርሽኝና የሕዝብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ምላሽ ሥራዎች ላይ በቀጥታ መሳተፋቸውንና ብቃታቸውንም እንዳረጋገጡ ጠቁመዋል።
ዶ/ር ጌታቸው አያይዘውም የፕሮግራሙ የመዋቅር ደረጃ የበለጠ፣ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ምደባ፣ የመስክ የአቅርቦት ወይም የሎጂስቲክስ ሰንሰለቶች፣ የጾታ ስብጥር እንዲሁም የበጀት ሁኔታዎች የበለጠ እንደሚጠናከሩ ጠቁመዋል። እነዚህንም በተመለከተም በቀጣይ 24 ወራት የሚተገበር ስድስት ዋና ዋና ነጥቦችን የያዘ የስትራቴጂክ ተግባር ዕቅድ ተዘጋጅቷል በማለት አስረድተዋል።
በጤና ሚኒስቴር የሰው ሀብትና ጤና ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ እና የEFELTP ዳይሬክተር አቶ አሰግድ ሳሙኤል፣ ግምገማው የፕሮግራሙን የ15 ዓመት ስራዎች ያሳየ እንደመሆኑ በቀጣይም ሊሰራባቸው የሚገቡ አቅጣጫዎችን ማመላከቱን የገለጹ ሲሆን በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኤባ ሚጄና በበኩላቸው በትምህርት ዘርፉ በመካሄድ ላይ ያለው ሪፎርም የሕብረተሰብ ጤና ምርምርን እና ቅድሚያ የሚገባቸው ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ለማጠናከር እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በስትራቴጂክ ዕቅዱ የአገር ውስጥ በጀትን ማጠናከር፣ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ተገቢ ምደባ ማረጋገጥ እና የሕብረተሰብ ጤና ክትትልና የወረርሽኝ መረጃ ሥርዓትን በይበልጥ ማዘመንን የሚሉ ነጥቦችን እንዳካተተ ከመድረኩ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን፣ በመድረኩ የEFELTP የ15 ዓመታት የግምገማ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን የግምገማው ግኝቶችና በፕሮግራሙ ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይም የፓነል ውይይት ተካሂዷል።
በመጨረሻም አጋር ድርጅቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የክልል ጤና ቢሮዎች የፕሮግራሙን ቀጣይ ሥራ በጋራ እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀርቧል።