ኢንስቲትዩቱ የማርበርግ ቫይረስን በመቆጣጠርና በመከላከል እረገድ ላበረከተው አስተዋጽዎ እውቅና ተሰጠው

ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሯን አስመልክቶ በተዘጋጀ የእውቅና መርሀግብር ላይ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለነበረው የማይተካ ሚና የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ አመስግነዋል::
ኢንስቲትዩቱ ቫይረሱ በሀገሪቱ መከሰቱን ተከትሎ የቫይረሱን አይነት መገምገም፣ እንዴት እንደሚተላለፍ መረጃ ማግኘት፣ የቫይረሱን ፣ ባህሪ እና የጂኔቲክ ልዩነት ማረጋገጥ ወይንም ሞሎኪውላር ልየታ እና ምርመራዎችን ከማከናወን ጀምሮ የበሽታ ቅኝቶችን በማከናወን እና ፈጣን ምላሽ በመስጠት ከፍተኛ ድርሻ እንደተወጣ የገለጹት ሚኒስትሯ በዘርፉ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ፣ የህብረተሰብ ጤና አደጋ በመከላከልና በመቆጣጠር እንዲሁም የህብረተሰብ ግንዛቤ በመፍጠርና በማሳተፍ ስራዎች (Risk Communication & Community Engagement) ፣ አቅምን በመገንባት ፣ ግብአትበማቅረብ፣ የሰው ኃይል በመመደብ፣ የቫይረሱ ስርጭት እንዲገታ ላደረገው አስተዋጾ እውቅና መሰጠቱን ተናግረዋል::
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለመቶ ዓመታት በጤናው ዘርፍ ሕብረተሰቡን ሲያገለግል የቆየ እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር መቅደስ ማርበርግን የመሰሉ በሽታዎችን ከፊት በመቅደም ከክልል ጤና ቢሮዎችና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ጋር በቅንጅት በመስራት ትልቁን ሚና የተጫወተ ተምሳሌት ነው ብለዋል::
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉን ጨምሮ ከፍተኛ የኢንስቲትዩቱ አመራሮችና ዳይሬክተሮች የህዝብ ተወካይች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ በተገኙበት የተቀበሉ ሲሆን ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እውቅናውን ተከትሎ እንደተናገሩት ኢንስቲትዩቱ እንደ ማርበርግ እና ኮቪድ የመሳሰሉ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ጠንካራ ስርዓት መዘርጋቱንና የተለያዩ ቫይረሶችንም ለመለየት የሚያስችል የላብራቶሪ አቅም መገንባቱን ገልጸው ከከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ መላው ሰራተኞችን፣ የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶችን በማሳተፍና ከአጋሮች ጋር በቅንጅት በመስራት የማርበርግ ቫይረስ በህብረተሰባችን ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ እንዲቀለበስ በከፍተኛ ኃላፊነት መወጣቱን አስረድተዋል::