የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ድንገተኛ ጤና አደጋዎች አስተዳደር የስድስት ወራት አፈጻጸሙ አበረታች መሆኑን አስታወቀ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የልህቀት ማእከል ለመሆን እየተጋ መሆኑን የስድስት ወራቱ አፈጻጸም በተግባር ያሳየ እንደሆነም ትነግሯል::
የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ቁጥጥር ዘርፍ የስድስት ወራት አፈጻጸምን የገመገመ ሲሆን የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በዘርፉ የተሰሩ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸው፣ ተቋሙ ወደ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየተጓዘ መሆኑን በተግባር መታየቱን አስታውቀዋል።
የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተሰሩ ስራዎች የተገኘው ውጤት በበሽታው ላይ የተወሰዱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እርምጃዎች፣ ፈጣን የምላሽ ቡድኖች ማቋቋም እና ከክልሎች ጋር በቅንጅት የተካሄዱ የክትትል ስራዎች መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በድንበር ላይ የጤና ቁጥጥር ማጠናከር፣ የማህበረሰብ ግንኙነት እና የስጋት ጊዜ ተግባቦት (Risk Communication and Community Engagement) ስራዎች በተቀናጀ መልኩ መከናወናቸው በበሽታው ስርጭት መቆጣጠር አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ተገልጿል። ይህ ተሞክሮ ለወደፊት ተመሳሳይ የቫይረስ ወረርሽኞች ምላሽ ለመስጠት የተሻለ ዝግጁነት መፍጠሩን ተናግረዋል።
የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶችን ማጠናከር እና የትንበያ ስራዎች ላይ ጥሩ አፈጻጸም መታየቱን የገለጹት ም/ዋና ዳይሬክተሩ የበሽታ መረጃ በዲጂታል ስርዓት እንዲሰበሰብ እና እንዲተነተን መደረጉ በፍጥነት ውሳኔ ለመስጠት አግዟል ብለዋል::
የስታቲስቲካዊ እና የኢፒዲሚዮሎጂ ሞዴሎችን በመጠቀም የሚኖሩ የበሽታ ስርጭቶችን አስቀድሞ መገመት በማስቻል ተግባራዊ ስራ መሰራቱ ተጠቅሷል።
ባለፉት ስድስት ወራት 1.8 ሚሊዮን በላይ በአፍ የሚሰጥ የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት እንዲሁም በሁለት ዙር 8.5 ሚሊዮን የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ለመስጠት ታቅዶ 8.8 ሚሊዮን መስጠት የተቻለ መሆኑን እና በድንገት የተከሰተው የማርበርግ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር አብዛኛው የስራ ትኩረት ወደዛ ቢያመራም ጎን ለጎን ግን የታቀዱ ስራዎችን መስራት መቻሉን የኢንስቲትዩቱ የቅኝትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መስፍን ወሰን በሪፖርታቸው አቅርበዋል።
አቶ ተመስጌን ለሚ የኢንስቲትዩቱ የተጓዦች እና ድንበር ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው ሪፖርት እንዳደረጉት በሁሉም መግቢያና መውጫ ኬላዎች በአጠቃላይ 3.8 ሚሊዮን በላይ አለም አቀፍ ተጓዦች ወደ ሀገር ሲገቡ አስፈላጊው የጤና ልየታ እንደተደረገላቸው፣ 679 ወደ ሀገር የመጡ እና 35 ወደ ውጭ ሀገር የሄዱ አስክሬኖች በዓለም አቀፍ ጤና ድንጋጌ መሰረት የጤና ቁጥጥር እንደተደረገላቸው እንዲሁም በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል የቢጫ ወባ ካለባቸው ሀገራት የመጡ ወደ 88 ሺህ ለሚጠጉ መንገደኞች የክትባት ሰርተፊኬት ማጣራት መደረጉን አስቀምጠዋል።
የሕብረተሰብ የጤና አደጋ የዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ሪፖርት በአቶ ዮሴፍ ንጉሴ እንዲሁም የሕብረተሰብ የጤና አደጋዎች ምላሽ እና መልሶ ማገገም ዳይሬክቶሬትን አጠቃላይ የግማሽ ዓመቱን የስራ አፈጻጸም ደግሞ በአቶ በላይነህ ኮኮቤ አቅርበዋል።
የአደጋ ዝግጁነት ሪፖርት እንዳመላከተው ከ332 ሚሊዮን ብር በላይ ለግብዓቶች ግዢ ከመንግስት እና ከባለድርሻ አካላት ማሰባሰብ መቻሉን፣ ከ79 ሚሊዮን ብር በላይ ለተከሰቱት የጤና አደጋዎች ምላሽ መዋሉን፣ ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ የመድሀኒትና የህክምና ግብዓት ግዢዎች ተፈጽመው ለተከሰቱት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ላይ መዋሉን እና ከ133 ሚሊዮን ብር በላይ ለአደጋ ምላሽ የሚሆን ግብዓቶች በግዢ ሂደት ላይ መሆናቸውን አመላክቷል።በተጨማሪም የኢትዮጵያ የአደጋ ጊዜ የሕክምና (Emergency Medical Team/EMT) ቡድን ከ50 በላይ ሀገር ውስጥ ተልእኮዎችን እንዳከናወነ፣ እናም በአሁኑ ጊዜ ከ600 በላይ የሰለጠኑ ባለሙያዎች በብሔራዊ የአደጋ ጊዜ የሕክምና ቡድን ዝርዝር ውስጥ መመዝገባቸውን እና ቡድኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊመዘገብ መቃረቡን መረጃዎች ያሳያሉ።
በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላም የቀሪ ዓመቱ ዕቅድ በቡድን በቡድን በመሆን ከተከለሰ እና ከቀተናጀ በኋላ ሁሉም የዘርፉ ዳይሬክቶሬቶች ዕቅዳቸውን አቅርበው በዶ/ር መልካሙ ማጠቃለያና ቀጣይ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።