የጸረ-ተህዋስያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድ (AMR) የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳን ያካተተ የጸረ-ተህዋስያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድ (#AMR) አስመልክቶ ምክክር እና አውደ-ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡
የኢንስቲትዩቱ የተላላፊ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት እና ወባና ትኩረት የሚሹ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት እንዲሁም አጋር ድርጅቶች አስተባባሪነት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር እና አራት የምስራቅ አፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ የሚሳተፉበት በመንግስትና በግል የሰውና የእንሰሳት መድሃኒት ፋርማሲዎች የጸረ-ተህዋስያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድን ከመከላከልና ከመቀነስ አንጻር ያላቸው ሚና የልምድ ልውውጥ አውደ-ጥናት ህዳር 4 እና 5/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
የአውደ ጥናቱ ዋና ዓላማ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የጸረ-ተህዋስያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድን ከመከላከልና ከመቀነስ አንጻር የሰውና የእንሰሳት የግልና መድሃኒት ፋርማሲዎች ሚናን ለማሳደግና እየተሰሩ ያሉ መልካም ተሞክሮዎችን የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ነው፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በአውደ ጥናቱ የመክፈቻ ፕሮግራም ወቅት እንደተናገሩት የጸረ-ተህዋስያን በጀርሞች መላመድ (AMR) በሰው እና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ስጋት እየሆነ መምጣቱን፣ ለዚህም የአንድ ጤና ትብብር በአራቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት እጅግ ወሳኝ በመሆኑ በርካታ ስራዎች በቅንጅት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም እንደ ኢትዮጵያ መንግስት የጸረ-ተህዋስያን በጀርሞች መላመድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል እስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን፣ በተለይም የአንድ ጤናን (ONE HEALTH) ማእቀፍን በመጠቀም ከዓለም ጤና ድርጅት(WHO) እና ከአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል (AFRCAN CDC) ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኢምባሲ ችግሩን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንፃር የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ሚስተር ሎረንት ሴራኖ በኢትዮጵ የፈረንሳይ እምባሲ ተወካይ በአውደ ጥናቱ ላይ እንደገለጹት አንድ ጤናን በመጠቀም የፀረ-ተዋስያን በጀርሞች መላመድን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር የአገራት ትብብርና የልምድ ልውውጥ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው አገራቸው ፈረንሳይ ለዘርፉ እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል፡፡
የጸረ-ተህዋስያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድን ለመከላከል የአንድ ጤና አተገባበር፣ አግባብ ያለው የመድሃኒት አጠቃቀም፣ ላቦራቶሪን መሰረት ያደረገ ቅኝት በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ፣ የግልና የመንግስት ፋርማሲዎች ሚናና መልካም ተሞክሮ በመድረኩ በተለያዩ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡