መሠረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና(Frontline-FETP) ያጠናቀቁ የጤና ባለሙያዎች የእዉቅና ሰርተፍኬት ተሰጣቸው

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ከኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ የስልጠና ማዕከል ጋር በመተባበር በአማራ ክልል ከተለያዩ ወረዳዎች ተወጣጥተው በሶስት ዙር መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና (Frontline-FETP) ላጠናቀቁ 37 የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም በኮምቦልቻ ከተማ የእዉቀና ሰርተፍኬት በመሰጠት አስመርቋል።
አቶ ጃፈር ከዛሊ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ተወካይ እንደገለጹት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የክልሎችን የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር አቅምን ለማሳደግ የመሠረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠናን ላለፉት አመታት ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል። በአጠቃላይ ስልጠናው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከአሁን ድረስ ከአማራ ክልል ለተወጣጡ ከ230 በላይ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሞያዎች ስልጠናው የተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ አወል ዳወድ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ባለሙያና የስልጠናው አስተባባሪ በሶስት ዙር መሰጠቱን የገለጹ ሲሆን የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቀድሞ የመለየት የመከላከልና ምላሽ የመስጠት ግንዛቤ እንዲሁም መሰረታዊ የኮምፒውተር ሞያዎች ጨምሮ ለባለሙያዎች በስፋት መሰጠቱን ገልጸዋል።
የብሔራዊ የስልጠና ማዕከል ማስተባበሪያ ተወካይ አቶ አስፋው ወሰን የስልጠና ማዕከሉን በተመለከተ ከተለያዩ የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተሮች ጋር በመሆን ከስልጠና ፋላጎት ዳሰሳ ጥናት ጀምሮ ፕላን በማድረግ ስልጠናዎች በማስተባበር እናም የስልጠናዎችን ጥራት ጠብቆ የስልጠና ቁሳቁሶችንና ሰነዶችን እንዲሁም ተከታታይነት ያለዉን የባለሙያ ምስክር ወረቀት በመሰጠት ላይ ይገኛል በማለት ተናግረዋል።
አቶ አንተነህ ደመላሸ የአማራ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ደሴ ቅርንጫፍ ዋና ዳይሬክተር እና አቶ አበበ ሲሳይ የአማራ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አደጋዎች ዝግጁነት ኬዝቲም ቡድን መሪ በእዉቅናዉ ሰርተፍኬት ላይ በመገኘት የእንኳን ደስ አላችሁ
መልዕክትና ሰልጣኞች ከስልጠናው ባገኙት ተጨማሪ እዉቀት ማህበረሰባቸዉን በተሻለና በተቀላጠፈ መልኩ እንዲያገለግሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።