በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጡ የጤና ቀውሶችን ለመከላከል የተቀናጀና ዘርፈ-ብዙ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአየር ንብረት ለውጥ፣ በስደትና በመፈናቀል እንዲሁም በሰው ልጅ ጤና መካከል ያለውን ቁርኝት የሚመለከተውን ሁለተኛውን ከፍተኛ ሴሚናር አካሂዷል።

ሴሚናሩ የአየር ንብረት ለውጥና መፈናቀል በምግብ ስርዓት፣ በስርዓተ-ምግብ፣ በበሽታዎች ስርጭት እና በጤና ሥርዓት ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ለመዳሰስ እና በጉዳዩ ላይ የምርምርና የፖሊሲ ምላሽን ለማጠናከር ያለመ ሲሆን፣ በመድረኩ የኖርዌይ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አማካሪና የላንሴት ኮሚሽን ተወካይ ፕሮፌሰር በርናዴት ኩማርን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
የኢንስቲትዩቱ የሥርዓተ-ምግብ፣ የአካባቢ ጤና እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማስረሻ ተሰማ እንዳስገነዘቡት በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጡ የጤና ቀውሶችን ለመከላከል የተቀናጀና ዘርፈ-ብዙ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።
ዶ/ር መስረሻ እንደገለጹት፣ አየር ንብረት ለውጥ ከአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ባለፈ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት እየሆነ ሲሆን፣ የበሽታዎችን ስርጭት፣ የምግብና የውሃ ዋስትናን እና የጤና ሥርዓትን የመቋቋም አቅም እየተፈታተነ ይገኛል። በተለይም የአየር ንብረት ለውጥና መፈናቀል በተመሳሳይ ጊዜ ሲከሰቱ በምግብ ስርዓት፣ በስርዓተ-ምግብ እና በበሽታዎች ስርጭት ላይ ውስብስብ አደጋዎችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። በመሆኑም ለእነዚህ ችግሮች ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት በምርምር፣ በፖሊሲና በተግባር የተቀናጀ አቀራረብ እንደሚያስፈልግ አስረድተው፣ ኢንስቲትዩቱ በተለይም ለአደጋ ተጋላጭና ተፈናቃይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ በመስጠት በጤና ጉዳዮች ላይ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።
የላንሴት የአየር ንብረትና ጤና ኮሚሽን (Lancet Commission on Climate and Health) የአፍሪካ አህጉራዊ የእውቀት ማዕከል አስፈላጊዎቹ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው እና ዝግጅት ተደርጎበት እንደሚቋቋም የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን ውሳኔውም ከኖርዌይ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (NIPH) እና ከዓለም አቀፍ የጤና መሪዎች ጋር ከተደረጉ ውይይቶች በኋላ የተደረሰበት መሆኑን ከሴሚናሩ ለመረዳት ተችሏል።
በኢንስቲትዩቱ፣ የወባ እና ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ገረመው ጣሰው በበኩላቸው፣ ኢንስቲትዩቱ ያለውን የጂኖሚክስ፣ የባዮኢንፎርማቲክስ እና የብሔራዊ መረጃ አስተዳደር ማዕከል መሠረተ ልማቶችን በማስተዋወቅ፣ አህጉራዊ የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህ ወደፊት የሚቋቋመው የእውቀት ማዕከል በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ አገራት ለሚገኙ ውሳኔ ሰጪዎች የምርምርና የጤና መረጃን ወደ ተግባራዊ ፖሊሲ ለመቀየር የሚያግዝ አህጉራዊ መድረክ ሆኖ ለማገልገል የታቀደ መሆኑ ተገልጿል።
የአፍሪካ አህጉራዊ የእውቀት ማዕከሉ መቋቋም በአየር ንብረት፣ በስደትና በጤና መካከል ያለውን ቁርኝት በተመለከተ የሚደረጉ ምርምሮችን በማጠናከር፣ የተመሠረተ መረጃ ለውሳኔ ሰጪዎች በማቅረብ እና የምርምር ግኝቶችን ወደ ፖሊሲና ተግባር ለማሸጋገር እንደሚያግዝ ይጠበቃል።