አረንጓዴ አሻራን ከጤና ጋር በማጣመር የአየር ንብረት ስጋትን ቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ ነው

የአየር ንብረት ሳይንስን ከሕብረተሰብ ጤናና ከሥነ-ምግብ ሳይንስ ጋር በማቀናጀት የቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ የትንበያና የዝግጁነት ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።

“A Centennial Legacy and Beyond: Transforming Risk Forecast into Health and Nutrition Action in Climate Impact Ethiopia” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው መድረክ፣ የአየር ንብረት መረጃና ትንበያን ከጤናና ከሥነ-ምግብ ውሳኔዎች ጋር በማገናኘት የሚከሰቱ የጤና ስጋቶችን ቀድሞ ለመለየት፣ ለመከላከልና ለመመለስ የተሰሩ ሥራዎች፣ የተገኙ ውጤቶችና የወደፊት አቅጣጫዎች ተመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ኢንስቲትዩቱ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያካበተውን የጤናና የሥነ-ምግብ ምርምር ልምድ በመጠቀም የአየር ንብረት ስጋቶችን ቀድሞ ለመለየት፣ ለመተንበይና ለመዘጋጀት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ከፍተኛ ሙቀትና የምግብ እጥረት በሕብረተሰቡ ጤና ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ለመቀነስ የምርምርና የትንበያ መረጃን ወደ ተጨባጭ የጤና እርምጃ መቀየር ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ዶ/ር መሳይ በንግግራቸው አረንጓዴ አሻራ የአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን የጤና ልማት አካል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች የአየር ጥራትን ከማሻሻል፣ የከተማ ሙቀትን ከመቀነስና የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠበቅ ባለፈ ለሕብረተሰቡ አካላዊና አእምሯዊ ደህንነት አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።
“አየር ንብረትና ጤና የተለያዩ ጉዳዮች ሳይሆኑ በአንድ የሕይወት ሰንሰለት የተሳሰሩ ጉዳዮች ናቸው” ያሉት ዶ/ር መሳይ፣ የአየር ንብረት ስጋትን መቀነስ የጤና ስጋትንም ቀድሞ መቀነስ መሆኑን አመልክተዋል።
በመድረኩ የቀረቡት ሳይንሳዊ ጥናቶችም በተለይ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች በአካባቢ፣ በአየር ንብረትና በሕብረተሰብ ጤና ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ለመረዳት ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ተገልጿል። በተለይም በከተሞች የሚከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ለአየር ንብረት መላመድ፣ ለአካባቢ ጤናና ለጤናማ ኑሮ ያላቸውን ሚና የሚያሳዩ ማስረጃዎች ቀርበዋል።
ዶ/ር መሳይ እንዳሉት፣ “አረንጓዴ አሻራ የምንተክለው ዛፍ ብቻ ሳይሆን፣ ለትውልድ የምንገነባው የጤናማ አካባቢና የተሻለ ሕይወት መሠረት ነው።” በመሆኑም የአረንጓዴ ልማትን ከጤና ልማት ጋር በማጣመር የአየር ንብረት-ተቋቋሚ የጤና ሥርዓት መገንባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፈጠነ ተሸመ በበኩላቸው፣ የአየር ንብረት ሳይንስን ወደ ጤና ትንበያና ውሳኔ ለመቀየር ተቋማዊ ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ኤልኒኖ ያሉ የአየር ንብረት ክስተቶች የውሃ ወለድ በሽታዎችን፣ ወባንና ሌሎች በሽታዎችን ሊያባብሱ በመቻላቸው፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያንና የጤና ሥርዓት ዝግጁነትን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የአየር ንብረት ለውጥ ከአካባቢ ጉዳይ ባለፈ ቀጥተኛ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት መሆኑን ጠቁመዋል። የአየር ንብረት፣ የጤናና የሥነ-ምግብ መረጃዎችን በማቀናጀት በጥናት፣ በቅድመ ትንበያና በፈጣን ምላሽ ላይ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
ኢንስቲትዩቱ ኮሌራ፣ ወባና ዴንጊ ትኩሳትን ጨምሮ በአየር ንብረት ሊባባሱ የሚችሉ በሽታዎችን ቀድሞ ለመተንበይና የላብራቶሪ አቅምን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑንም ዶ/ር ጌታቸው ገልጸዋል።
የሥርዓተ-ምግብ፣ አካባቢ ጤና እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማስረሻ ተሰማ መድረኩ የአየር ንብረት ቅኝትንና ሳይንሳዊ ምርምርን በማገናኘት የጤና ስጋቶችን ቀድሞ ለመለየትና ለመከላከል የሚያስችል መፍትሄ-ተኮር መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህን የተቀናጀ ሥራ በተሳለጠ መልኩ ለማስኬድ “የአየር ንብረት፣ ጤና እና አመጋገብ የዕውቀት ማዕከል” ተቋቁሞ በኢንስቲትዩቱ መሪነት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በጥምረት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
ማዕከሉ የአየር ንብረት፣ ጤናና ሥነ-ምግብ መረጃዎችን በማጣመር ለውሳኔ ሰጪዎችና ለጤና ሥርዓቱ ቀድሞ የሚያስጠነቅቁ ሳይንሳዊ መረጃዎችን ለማቅረብ እንዲሁም ምርምርን ወደ ተግባራዊ የጤና እርምጃ ለመቀየር የሚያግዝ መድረክ መሆኑ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም በመድረኩ የቀረቡ ጥናቶች በተለይ በአዲስ አበባ በኮሪደር ልማት የተከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች በአካባቢ ጤናና በአየር ንብረት መላመድ ላይ ያላቸውን አዎንታዊ አስተዋፅኦ ያሳዩ መሆናቸው ተገልጿል።
የአረንጓዴ አሻራን በማበረታታት የሕብረተሰብ ጤናን ለማጠናከር የተያዘውን ቁርጠኝነት በተግባር ለማሳየትም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተርና ም/ዋና ዳይሬክተሮች በኢንስቲትዩቱ ግቢ ውስጥ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ እፅዋትን ተክለዋል።
በአጠቃላይ፣ የአየር ንብረት መረጃን ወደ ተጨባጭ የጤና እርምጃ መቀየር፣ ምርምርን ማጠናከር፣ የአረንጓዴ ልማትን ማስፋፋትና ተቋማዊ ቅንጅትን ማሳደግ አየር ንብረት-ተቋቋሚ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ቁልፍ መሆኑ ተገልጿል።