ኢንስቲትዩቱ ከአሶሴሽን ኦፍ ፐብሊክ ሄልዝ ላቦራቶሪ ጋር በመሆን የLaboratory Statistical Quality Control and Method Verification ስልጠና ሰጠ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአሶሴሽን ኦፍ ፐብሊክ ሄልዝ ላቦራቶሪ (Association of Public Health Laboratories/APHL/) ጋር በ Laboratory Statistical Quality Control and Method Verification ላይ ለሁለት ሳምንት የቆየ ስልጠና በአዳማ ከተማ ለጤና ላቦራቶሪ ባለሙያዎች የሰጠ ሲሆን፣ በስልጠናው ላይ ከዚህ ቀደም በISO 15189፡2012 መስፈርቶች ላይ እውቅና ያገኙ ላቦራቶሪዎች እና ከሌሎች አዳዲስ የጤና ተቋማት የተውጣጡ የላቦራቶሪ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሮ አብደላ በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላቦራቶሪ አክሪዲትሽን(ዕውቅና) ስራዎች ዋና የትኩረት አቅጣጫ (ፍላግ-ሽፕ) መሆኑን የገለጹ ሲሆን አያይዘውም የጤና ላቦራቶሪዎች የሚሰጡትን አገልግሎት ጥራት ለማስጠበቅ፣ የተገልጋይን እርካታ ለመጨመርና አለም አቀፍ የISO 15189፡2022) እውቅና እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር ኢንስቲትዩቱ አስፈገላጊውን ድጋፍ እና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ለዚህ ስልጠና መሳካት ትልቁን ድጋፍ ያደረገውን APHL ያመሰገኑ ሲሆን እንዲሁም ሌሎች ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመሆን እየተሰሩ ላሉ የላቦራቶሪ አቅም ግንባታ ስራዎችም ለAPHL፣ ለCDC-Ethiopia እና ሌሎች አጋር አካላትን አመስግነዋል ፡፡ የላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳይሪክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል መለስ በበኩላቸው የተዘጋጀው የተግባር ስልጠና የጤና ተቋማት የላቦራቶሪ ምርመራ ዘዴዎች የሚጠበቅባቸውን የጥራት ደረጃ ማሟላታችውን ለማረጋገጥና ያሉ ክፍተቶችን ለማረም ያለው ሚና የጎላ መሆኑን የስልጠና መዝጊያ ላይ የገለጹ ሲሆን እንዲሁም ሰልጣኞች የሰለጠኑትን ስልጠና በፍጥነት ተግባር ላይ እንዲውሉ መልዕክት አስተላለፈዋል።
ዶ/ር ዮሃንስ መንግስቱ የAPHL ኢትዮጵያ ፕሮግራም ዳይሬክተር በበኩላቸው እንዳስረዱት በተመረጡ የጤና ላቦራቶሪዎች የሚሰጠዉ የላቦራቶሪ አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆንና አለም አቀፍ እውቅናም እንዲያገኙ ሌሎች ተጨማሪ ስልጠናዎችንና ሌሎች ድጋፎችን ተቋማቸው አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡