ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ መሠረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ያጠናቀቁ የጤና ባለሙያዎች ሰርተፍኬት ተቀበሉ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ከኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ የስልጠና ማዕከል ጋር በመተባበር ከተለያዩ ክልሎች ተውጣጥተው በሶስት ዙር መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና (Frontline-FETP) ያጠናቀቁ ከ40 በላይ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎችን ሰኔ 26/2017 ዓ.ም በአዳማ ከተማ አስመርቋል፡፡
ወ/ሮ ነኢማ ዘይኑ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ይህ ፕሮግራም በተለያዩ የጤና አደጋዎች የቅድመ ክትትልና ምላሽ ስራዎች ላይ ያለው ከፍተኛ አስተዋፅዖ በተግባር የተረጋገጠ መሆኑንና የአሁኑን ዙር ስልጠና ደግሞ ለየት የሚያደርገው ሰልጣኞቹ ከተለያዩ ዘጠኝ ክልሎች የተወጣጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የዳይሬክቶሬቱ የፈጣን ምላሽ ቡድን ዲቪዥን ኃላፊ ዶ/ር መልካሙ አስራት በበኩላቸው ሰልጣኞች ከተለያዩ ክልሎች የመጡ በመሆናቸው ያላቸውን የተለያዩ ልምዶች እርስ በርሳቸው እንዲለዋወጡ ያስቻለ ስልጠና እንደነበረ ተናግረው በመቀጠልም ስልጠናው በስልጣኞች ላይ ያመጣውን ተግባራዊ ለውጥ ለማረጋገጥ የክትትል ስራ እንደ ሚሰራና ለቀጣይ ስልጠናዎች መጠናከር ያለባቸው ጉዳዮች እንደሚጠናከሩ አስታውቀዋል።
አቶ አወል ዳውድ የዳይሬክቶሬት ባለሙያና የስልጠናው አስተባባሪ ስልጠናው በሶስት ዙር መሰጠቱን የገለጹ ሲሆን የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ቀድሞ የመለየት የመከላከልና ምላሽ የመስጠት ግንዛቤን እንዲሁም መሰረታዊ የኮምፕዩተር ሞያዎችን ጨምሮ ለባለሙያዎቹ በሶስት ዙር በስፋት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡