የስደት ተመላሾች ምላሽ አሰጣጥን አስመልክቶ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተካሄደ

የኢንስቲትዩቱ የተጓዦችና የድንበር ጤና ዳይሬክቶሬት የስደት ተመላሾችን አስመልክቶ ለስድስት ወራት ሲከናወኑ የቆዩ የምላሽ አሰጣጥ ስራዎችን ጥር 3 እና 4/2017 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተካሄደ ።
የግምገማ መድረኩ ዋና አላማ ያለፉትን ስድስት ወራት የተከናወኑ የእቅድ አፈጻጸምን በተመለከተ የነበሩ ውጤታማ ተግባራትን እና የነበሩ ክፍተቶችን የመለየት ብሎም የጋራ መግባባት በመፍጠር የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ነው፡፡
በተደረገው የግምገማ መድረክ በስድስት ወራት የተከናወኑ የስራ ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን የተመዘገቡ ውጤታማ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንዲሁም ክፍተት የታየባቸውን አፈፃፀሞች በተመለከተ የቀጣይ ተግባራዊ እቅድ እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር ሙሉ ኃላፊነቱን ከተረከበበት ከነሐሴ 26/2015 ዓ.ም ጀምሮ ሲያከናወን እንደ ቆየው በአሁኑ ሰዓት በሳውዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙትን ከ50 ሺ በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ዜጎች ወደ አገራቸው ለማስመለስ አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ እየተደረገ መሆኑን እና ወደ አገራቸው የማሰመለሱ ስራ በቀጣይ ቀናት እንደሚጀመር ከግምገማ መድረኩ መረዳት ተችሏል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ የፌዴራል ሆስፒታሎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ስር የሚገኙ ሆስፒታሎች፣ የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) እንዲሁም የተለያዩ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች በግምገማ መድረኩ ላይ ተሳትፈዋል፡፡